ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የየመን ተገንጣይ ቡድን የኤደንን ወደብ ተቆጣጠረ
የየመን ተገንጣይ ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚደገፈው መንግሥት ጋር ውጊያ በማድረግ የኤደንን ወደብ መቆጣጠራቸው ይፋ አድርገዋል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚደገፈው የደቡባዊ ሽግግር ምክር ቤት (ሳውዘርን ትራንዚሽናል ካውንስል) ደቡባዊውን የመን ነፃ መንግሥት ለመመስረት የሚታገሉ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም የጦር ሰፈሮችንና ቤተ መንግሥቱን መቆጣጠራቸውን ይፋ አድርገዋል።
በሌላ በኩል በሳዑዲ የሚመራው የጥምረት ኃይል በበኩሉ አፀፋዊ ወታደራዊ ምላሽ መስጠታቸውን ይፋ አድርገዋል።
መንግሥት የተገንጣዩ ቡድን ወደቡን መቆጣጠር "መፈንቅለ መንግሥት" ነው ብሎታል።
የጥምር ኃይሉ የደቡባዊ ሽግግር ምክር ቤቱ የኤደንን ወደብ በአስቸኳይ እንዲለቅ መልእክት በማስተላለፍ፤ ይህ ተግባራዊ ካልሆነ አፀፋዊ ምላሽ እንደሚጠብቃቸው ገልጿል።
የሽግግር ምክር ቤቱ የኤደንን ወደብ ከተቆጣጠረ በኋላ ሁለቱ ሃይሎች ተኩስ የማቆም ስምምነት ቢያደርጉም ነገሮች እስካሁን የጠራ መልክ እንደሌላቸው ተገልጿል።
ደቡባዊ የኤደን ወደባዊ ከተማ ለፕሬዚዳንት አብድራቡህ መንግሥት ጊዜያዊ መቀመጫ ነበረች።
ፕሬዚዳንቱ በአሁኑ ወቅት በሳዑዲዋ መዲና ሪያድ መቀመጫውን አድርጓል።
የተገንጣዩ ቡድን ከፍተኛ ኃላፊ ቅዳሜ እለት ቤተ መንግሥቱን ሲቆጣጠሩ ያለምንም ውጊያ እንደሆነ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
"በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ሁለት መቶ የሚሆኑ ክብር ዘቦችን በሰላም እንዲወጡና እንዲያልፉ አድርገናል" በማለት ኃላፊው ተናግረዋል።
አንድ የአይን እማኝ በበኩሉ ቤተ መንግሥቱን ያለምንም ትግል እንዳስረከቧቸው ለዜና ወኪሉ ተናግሯል።
ከዚህም በተጨማሪ የሃገሪቱ ባለስልጣን እንደተናገሩት ተገንጣዮቹ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ቤት እንዲሁም የጦር ሰፈሮችን እንደተቆጣጠሩ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገንጣዩን ቡድን ድርጊት "በአለም አቀፍ ዘንድ እውቅና ያለው መንግሥትና ተቋማት ላይ የተደረገ መፈንቅለ መንግሥት" ብሎታል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የተገንጣዩን ቡድን ያሰለጠነችወ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ነገሮች እንዲረጋጉ ጥሪ አቅርባለች።
ዶክተርስ ዊዝ አውት ቦርደርሰ የተባለው ድርጅት በበኩሉ የኤደንን ወደብ ከተማ "የጦርነት አውድማ" ያላት ሲሆን ሆስፒታሎቿም ማስተናገድ ከሚችሉት በላይ መለጠጣቸውን ገልፀዋል። ከሀያ አራት ባነሰ ሰአታትም ውስጥ 119 ግለሰቦችን እንዳከሙ አስረድተዋል።
ከሰባ በላይ የሚሆኑ ሰዎችም እንደተገደሉ የየመንን የፀጥታ ኃይሎችን ዋቢ አድርጎ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
በየመን የርስ በርስ ጦርነት ሺዎች ተገድለዋል፤ ብዙዎችም በምግብና በህክምና እጦት እንዲሰቃዩ ምክንያት ሆኗል፤ በአጠቃላይ ለሃገሪቱ መውደም ምክንያት ሆኗል።