በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ከስዊዘርላንድ ድንበር እንዲመለሱ ተደረገ

17ኛው የኢትዮጵያዊያን ፌስቲቫል በዙሪክ

የፎቶው ባለመብት, Empics

ታትሟል

17ኛው የኢትዮጵያ ባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል በስዊዘርላንድ ዙሪክ በድምቀት እየተካሄደ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

በፌስቲቫሉ ላይ ለመሳተፍ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት የተሰባሰቡ ሲሆን ከኢሚግሬሽን ጋር በተያያዘ ምክንያት ብዙዎች ወደ ስዊዘርላንድ መግባት ሳይችሉ መቅረታቸው ተሰምቷል።

ስዊዘርላንድ የምትከተለው ጥብቅ የሆነ የድንበር ቁጥጥር ከፈረንሳይ እና ከጀርመን የሄዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የበዓሉ ተሳታፊዎችን ጨምሮ ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራት የሄዱ ከድንበር እንዲመለሱ አስገድዷል።

በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ ጉዞ ጀምረው ከድንበር እንዲመለሱ የተደረጉ ሰዎች ቁጥር በውል ባይታወቅም፤ ብዙዎቹ በባቡር፣ በአውቶቡስ እና የራሳቸውን መኪና በማሽከርከር የወደ ዙሪክ ያመሩ ነበሩ ተብሏል።

ከድንበር እንዲመለሱ ከተደረጉ ሰዎች መካከል በሚኖሩበት ሃገር የጥገኝነት ጥያቄያቸው ገና ምላሽ ያላገኘ እንዲሁም በሚኖሩበት ሃገር የመኖሪያ ፍቃድ እንጂ ዜግነት ያልተሰጣቸው ሰዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ከፈረንሳይ የመጣው የኢትዮ ማርሴል ቡድን እንዲሁም የጀርመኑ ኢትዮ ፍራንክፈርት ቡድኖች አባላት በከፈል ከድንበር እንዲመለሱ ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ የስፖርት እና ባህል ፌስቲቫል በአውሮፓ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ አሳየኸኝ ጥላሁን፤ ከአሁን በኋላ ይህ ፌስቲቫል የሚዘጋጅበት ሃገር በጥንቃቄ እንድንመርጥ ትምህርት ሰጥቶናል ሲሉ ተናግረዋል።

በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ወደ 40ሺህ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ አሳየኸኝ "በእንግሊዝ እስካሁንም ውድድሩን ማዘጋጀት ያልተፈለገበት ምክንያት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መግባት አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፤ በስዊዘርላንድም መሰል ችግር ገጥሞናል ከአሁን በኋላ ዝግጅቱ የሚካሄድበትን ሃገር በጥንቃቄ እንደንመርጥ ትምህርት ሰጥቶናል" ብለዋል።