ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለሳቸው ተገለፀ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ተፈናቅለው የነበሩት ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለሳቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው ለቢቢሲ አስታወቁ።
ይሁን እንጂ ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ 500 የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው ጠገዴ ወረዳ 'ሶሮቃ' በሚባል ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በግጭቱ ምከንያት ወደ 3500 ገደማ ቤቶች መቃጠላቸውን የሚያስታውሱት ኃላፊው በመንግሥት ደረጃ ወደ 3200 የሚጠጉ ቤቶችን መልሶ በመገንባት ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን አስረድተዋል።
ኃላፊው እንደሚሉት እነዚህ ቤቶች መልሰው ሲገነቡ እንጨት የሚያቀርቡት ራሳቸው ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ሲሆኑ ሌሎች ቁሳቁሶች ግን የሚሟሉት በመንግሥት ነው።
በመሆኑም ግንባታቸው ያልተጠናቀቀው 300 ቤቶች ባለቤቶች እንጨት ማቅረብ ባለመቻላቸው ሳይሠራላቸው መቆየቱን ይናገራሉ።
አሁን ላይ ግን መንግሥት በጀት ይዞ፤ የእነርሱንም ቤት አጠናቆ ለማስረከብ የእንጨት ግዥ እየተከናወነ እንደሆነ ነግረውናል።
ከዚህም በተጨማሪ መሠረታዊ የሆኑ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደተደረገም አቶ መንበሩ ገልፀዋል።
ከክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና እና ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር የእርሻ ቁሳቁሶችን ለአርሶ አደሩ ማካፋፈል ተችሏል። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ከመብዛቱ የተነሳ ምርጥ ዘር የማቅረብና የበሬ ኪራይ የመክፈል አንዳንድ ክፍተቶች እንዳሉ ኃላፊው አልሸሸጉም።
"ያሉባቸው ችግሮች ሙሉ በሙሉ ተፈትተዋል ማለት አይቻልም" የሚሉት ኃላፊው ተፈናቃዮቹ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ከሆነ ከ'ሶሮቃ' በስተቀር ተፈናቃዮች ይገኙባቸው የነበሩ መጠለያ ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል። ለተፈናቃዮቹ የሚደረገው የምግብ ድጋፍ ግን አሁንም ባሉበት እየተሠጠ መሆኑን አክለዋል። ይህ ድጋፍም ምርት እከሚያመርቱበት ታህሳስ 2012 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
አካባቢው ወደ ቀድሞ ሰላሙ እንዲመለስ መከላከያና የክልሉ የፀጥታ ኃይል በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በአጠቃላይ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንድር ዞን የተመዘገቡ 82 ሺህ ተፈናቃዮች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በማዕከላዊ ጎንደር፤ አይምባ፣ ትክል ድንጋይ፣ ጯሂት፣ ቆላ ድባ፣ አርባባ፣ ምስራቅ በለሳ፣ ስላሬ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች በአጠቃላይ 49700 ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደነበር ይታወሳል።