በዚህ ሳምንት ምን እንጠብቅ? ከአዲስ አበባ እስከ አሜሪካ
ሰኞ ነው። የሳምንቱ መጀመሪያ የሥራ ቀን። በዚህ ሳምንት በቀጠሮ ከተያዘላቸው ኹነቶች መካከል አራቱ፡
1. ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ዛሬ ሰኞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ዓመታዊ የመንግሥት አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሪፖርቱን ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባሉ ተብሎ የተጠበቀው የዛሬ ሳምንት ነበር። ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ እና በባህርዳር የተከሰቱ የመንግሥት ባለስልጣናት ግድያን ተከትሎ ወደ ዛሬ እንዲሸጋገር ሆኗል።
2. ለአሜሪካ ሰላምታ እንሰጣለን
አሜሪካውያን በየዓመቱ ጁላይ 4 (ሰኔ 27) ከብሪታኒያ ነጻ የወጡበትን የነጻነት ቀን ያከብራሉ። የፊታችን ሃሙስ በሃገረ አሜሪካ በገፍ ይበላል፣ ቢራ ይጠጣል፣ ርችት ይተኮሳል፣ የሙዚቃ ድግሶች ይኖራሉ ብቻ ፌሽታ ይሆናል።
ከወራት በፊት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጁላይ 4 ዕለት ''በዋሽንግተን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ በርካታ ህዝብ ይሰበሰባል'' ብለው ነበር። ትራምፕ ''ዕለቱም 'ሰላምታ ለአሜሪካ' ይባላል። ከምትወዱት ፕሬዝደንታችሁም ንግግር ትሰማለችሁ'' ሲሉ ተናግረው ነበር።
3. በርካታ ስፖርታዊ ውድድሮች ይኖራሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች መካሄዳቸውን ይቀጥላሉ። በግብጽ እየተካሄድ የሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ መጠቃለያ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
የአፍሪካ ዋንጫ ብቻ አይደለም፤ ዌምበልደን የቴኒስ ውድድር ዛሬ ሰኞ ይጀምራል። የፊታችን ቅዳሜ ደግሞ ተወዳጁ የብስክሌት ውድድር፤ ቱር ደ ፈራንስ በቤልጄም ይጀምራል። የሴቶች የዓለም ዋንጫም በፈረንሳይ ይቀጥላል።
4) ግሪክና ዴሞክራሲ
በሚቀጥሉት ቀናት ግሪክ ዴሞክራሲ የውልደት ቦታ ስለመሆኗ የሚገልጹ ብዙ መረጃዎች እንደሚወጡ ይጠበቃል። በመጪው እሁድ ሃገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ የምታካሂድ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ 2015 በኋላ የመጀመሪያው ነው።












