በኦሮሚያ ምሥራቅ ሸዋ ሉሜ ወረዳ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ተከሰከሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታትሟል
ዛሬ ረፋድ ላይ በምሥራቅ ሸዋ ሉሜ ወረዳ አንድ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ የ18 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።
ሄሊኮፕተሩ ከድሬዳዋ ወደ ቢሾፍቱ በመብረር ላይ ነበር ተብሏል።
ተሳፋሪዎቹ በሙሉ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን 15ቱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ እና 3ቱ ደግሞ ሲቪሎች መሆናቸውን የአገር ቤት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ኢቢሲ የፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ከሟቾቹ ሁለት ሴቶችና ሁለት ሕጻናት ይገኙበታል።
ሄሊኮፕተሩ የተከሰከሰው ወደ መዳረሻው ቢሾፍቱ ለመድረስ የ20 ደቂቃ በረራ ሲቀረው ነበር። በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች እንተናገሩት ሄሊኮፕተሩ በጥቅጥቅ ቁጥቋጦ ውስጥ ከመከስከሱ በፊት በእሳት ተያይዞ ነበር።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ይዘው የወጡት የአደጋው ምስል፤ የሄሊኮፕተሩ አካላት በጥቅጥቅ ቁጥቋጦ ውስጥ ተበታትነው ያሳያል።
የአደጋው ምንስዔ እየተጣራ ነው ተብሏል።








