የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኖርዌይን ከቻይና በዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ሊያገናኝ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕቃ ማጓጓዣ አውሮፕላን ኦስሎና ጓዋንዡን ያገናኛል
ታትሟል

በኢሲያ እያደገ የመጣውን የባሕር ውስጥ ምግብ ፍላጎት ለማርካት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአሳ ምርቶችን ከኖርዌይ ወደ ቻይና ማጓጓዝ ሊጀምር ነው።

ከመጪው መስከረም ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር መንግድ በቦይንግ 777 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ኖርዌይ መዲና ኦስሎ ካቀና በኋላ ወደ ቻይነዋ ጓዋንዡ ይጓዛል።

ዕቃ አጓጓዡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በረራውን የሚያደርግ ሲሆን፤ ይህም ግዙፍ በሆነው ሰሜናዊ አውሮጳ ገበያ ውስጥ ድርሻ እንዲኖረው ያስችለዋል።

አየር መንገዱ ይህን በረራ ማድረጉ ለኖርዌይ የአሳ ምርት ኢንዱስትሪ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ተብሎ የታመነበት ሲሆን፤ አዲሱ በረራ ኖርዌይን ለቻይና የአሳ ምርት ከሚልኩት አገራት ተመራጭ እንደሚያደርጋት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለበርካቶች የሥራ ዕድልን መፍጠር ይችላል ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከኦስሎ ወደ ጉዋንዡ የሚጀምረው በረራ በዕቃ ማጓጓዝ ዘርፉ ላይ የተካነ አገልግሎት አቅራቢ ተቋም ስለመኾኔ ይመሰክርልኛል ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በኦስሎ አውሮፕላን ማረፊያ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ዕቃ ላኪ እና ተቀባይ ድርጅቶች አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ እንደሚያበረታታ አስታውቋል።