ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በምክር ቤት አፈ ጉባኤ መኖሪያ ቤት ላይ ድንገተኛ ብርበራ አደረገ
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩትን የአገሪቱ ምክር ቤት አፈ ጌባኤ መኖሪያ ቤት ላይ ድንገተኛ ብርበራ አደረገ።
አፈ ጉባኤል ማፒሳ ናኩላ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የሥራ ውል ለመስጠት ጉቦ ጠይቀዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኘው የአፈ ጉባኤዋ መኖሪያ ቤት ላይ ብርበራው ከተፈጸመ በኋላ የአገሪቱ ምክር ቤት ማፒሳ ናኩላ የቀረበባቸውን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጋሉ ሲል አፈ ጌባኤዋን ተከላክሏል።
ምክር ቤቱ ጨምሮም አፈ ጉባኤዋ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ፍተሻ ሲደረገ ተባባሪ እንደነበሩ ገልጿል።
ፖሊስ ድንገተኛውን ብርበራውን ያደረገው ፍተሻ እንዲደረግ ዐቃቤ ሕግ ከፍርድ ቤት ፍቃድ ካገኘ በኋላ መሆኑ ተሰምቷል።
የ67 ዓመቷ ፖለቲከኛ የአገሪቱ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት እአአ 2021 ላይ የነበረ ሲሆን ከዚያ በፊት ለ9 ዓመታት መከላከያ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።
ቢዝነስ ደይ የተባለ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ማፒሳ ናኩላ መከላከያ ሚኒስትር ሳሉ አንድ ኩባንያ ጦር መሳሪያዎችን ለማንቀሳቀሰ የወጣውን ጨረታ ለመውሰድ 120ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል።
የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሲረል ራማፎሳ እአአ 2018 ላይ ወደ ስልጣን ሲመጡ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና ለመታገል እንደሚሰሩ ቃል ገብተው ነበር።
አፈ ጉባኤዋም ቢሆኑ “ሙስና በዴሞክራሲ እና በመልካም አስተዳደር መርሆች ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር መሆኑን” ያምናሉ ይላል ፓርላማው ያወጣው መግለጫ።
“ስለዚህም በእንደዚህ ባለ ውንጀላ በጣም ተረብሸዋል” ሲል የምክር ቤቱ መግለጫ አክሏል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በምክር ቤት አፈ ጉባኤዋ መኖሪያ ቤት ላይ ብርበራ መካሄዱን ቢያረጋግጥም ክስ ይመሰረትባቸው እንደሆነ ያለው ነገር የለም።