"የመጨረሻ ዓመቴ ሊሆን ይችላል" - ሮናልዶ ጫማ እንደሚሰቅል ጠቆመ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አንጸባራቂ የእግር ኳስ ዓመታትን ያሳለፈው ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ይህ የውድድር ዘመን በተጫዋችነት የሚቀጥልበት የመጨረሻው ዓመት ሊሆን እንደሚችል ጠቆመ።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ከረጅም ጊዜ አጋሩ ጆርጂና ሮድሪጌዝ ጋር ጋብቻ የፈጸመው የ41 ዓመቱ ሮናልዶ፣ የወደፊት ሕይወቱን ቤተሰቡ ላይ ያተኮረ ለማድረግ እያሰበ መሆኑን ገልጿል።

የአምስት ባሎንዶር እና አምስት የቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ሮናልዶ፣ በእንግሊዝ፣ ስፔን፣ ጣሊያን እና ሳውዲ ዓረቢያ ሊጎች ዋንጫ ማንሳት ችሏል። በወንዶች ዓለም አቀፍ እግር ኳስ የምንግዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።

የፖርቹጋሉ አምበል አራት ዓመታትን ካሳለፈበት የሳውዲ ፕሮ ሊግ ቻምፒዮኑ አል ናስር ጋር የተፈራረመው ውል ሊጠናቀቅ የአንድ ዓመት ጊዜ ይቀረዋል።

ሮናልዶ የፈጸመውን ጋብቻ በተመለከተ ለቮግ መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ፣ "ምናልባትም ይህ የመጨረሻው የእግር ኳስ ዓመቴ ነው፤ እጅግ አስደናቂ የሆነ ሌጋሲ ማኖር እፈልጋለሁ" ብሏል።

"የወደፊት የሕይወቴ አቅጣጫው በሙሉ ተሰምሯል። [በሥራ] እንድጠመድ የሚያደርጉኝ በርካታ ነገሮች ስላሉ አንድ ነገር ብቻ መጥቀስ ይከብደኛል። እግር ኳስ ትልቅ ክፍተት ሊፈጥር ስለሚችል፣ ጊዜሽን በአንድ መንገድ ብቻ ሳይሆን በበርካታ መንገዶች መሙላት ይኖርብሻል" ሲል ተናግሯል።

"የበለጠ ደስታ፣ የበለጠ ጉዞ ይኖረኛል፤ እጅግ የምወደውን ፈጣን የቴኒስ ጨዋታ (ፓዴል) መመልከት እና መጫወት እንዲሁም እንዲሁም ያገኘሁትን፣ ያገኘነውን ማጣጣም መቀጠል" ሲል ሕይወቱ ምን ሊመስል እንደሚችል ጠቁሟል።

"ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ በርካታ መስዋዕትነቶች የተከፈለባቸው 25 ዓመታት ነበሩ" ብሏል።

ሮናልዶ 1,000 ግቦችን ያስቆጠረ አንጋፋ ተጫዋች ለመሆን 24 ግቦች ብቻ ይቀሩታል።

የረጅም ጊዜ ተቀናቃኙ እና ስምንት ጊዜ የባሎንዶር ሽልማትን በማሸነፍ ሪከርድ የያዘው ሊዮኔል ሜሲ፣ ከአሁን በኋላ ለምን ያህል ጊዜ እግር ኳስ መጫወት እንደሚቀጥል እርግጠኛ አለመሆኑን በቅርቡ ተናግሯል።

የሁለቱ ተጫዋቾች የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ የተለያየ አቅጣጫን ይዟል። በሮናልዶ አምበልነት የሚመራው የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን በ16ቱ ዙር ከውድድሩ ተሰናብቷል። ሜሲ ደግሞ ስምንት ግቦችን በማስቆጠር አርጀንቲናን ለፍጻሜ አብቅቷል።

ሮናልዶ ሐምሌ ላይ ስድስተኛ ጊዜ የተሳተፈበት የአሁኑ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው እንደሆነ ለቀረበለት ጥያቄ፣ "በተረጋጋ አዕምሮ" ከቤተሰቡ ጋር እንደሚወያይ ተናግሮ ነበር።

አል ናስር የሳውዲ ፕሮ ሊግ ዋንጫውን ለማስጠበቅ ቅዳሜ ዕለት ከአል ፋተህ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ሮናልዶ አልተሳተፈም፤ ነገር ግን ከቤተሰቡ ጋር በስቴዲየም ተገኝቶ ቻምፒዮኖቹ ሲያሸንፉ ተመልክቷል።