አርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ ሲያሸንፉ ዩናይትድ በሜዳው ሽንፈት ገጥሞታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ በማሸነፍ በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ሲቀጥሉ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ተሸንፏል።
አርሰናል በሜዳው ኒውካስልን አስተናግዶ 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል።
መድፈኞቹ የበላይነታቸውን ባሳዩበት ጨዋታ ስድስተኘውን ተከታታይ የሊግ ጨዋታቸውን አሸንፈዋል።
የኒውካስሉ ስቨን ቦትማን በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠራት ኳስ የለንደኑ ቡድን የመጀመሪያ ጎሉን አግኝቷል።
ጫናቸውን ያጠናከሩት መድፈኞቹ ካይ ሃቨርትዝ ሁለተኛዋን ጎል አስቆጥሯል።
ጨዋታው 2 ለ 0 በሆነ ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ ቡካዮ ሳካ እና ጃኩብ ኪዊዮር ባስቆጠሯቸው ግቦች አርሰናል 4 ለ 0 መምራት ችሏል።
በጨዋታው መገባደጃ ላይ ጆ ዊሎክ ቡድኑን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ የማይክል አርቴታ ቡድን ከሊጉ መሪ ሊቨርፑል በሁለት ነጥብ ብቻ ርቆ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል።
ማንቸስተር ሲቲም ቅዳሜ በተደረገው የሊጉ ጨዋታ በርንመዝን በማሸነፍ ሦስት ነጥቦችን አሳክቷል።
ጨዋታውን በተቀዛቀዘ ሁኔታ የጀመረው ሲቲ አማካዩ ፊል ፎደን ባስቆጠራት ጎል ማሸነፍ ችሏል።
በዚህም ሲቲ ከሊጉ መሪ ሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ርቆ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ችሏል።
በ26ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በሜዳው ፉልሃምን ያስተናገደው ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸነፈ።
በጉዳት መሰለፍ ያልቻለውን ራስመስ ሆይሉንዱን ያጣው ዩናይትድ የአጥቂ መስመሩ ደካማ ሆኖ አምሽቷል።
ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያውን አጋማሽ ያለ ጎል አጠናቀዋል።
በተደጋጋሚ ወደ ግብ የቀረቡት ፉልሃሞች በካልቪን ባሲ ግብ ቀዳሚ መሆን ችሏል።
የዩናይትዱ ተካላካይ ሃሪ ማጓየር በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር።
አሌክስ ኢዮቢ በተጨማሪ ሰዓት ባስቆጠራት ግብ ፉልሃም ሦስት ነጥቡን እንዲወስድ አስችሎታል።
በሳምንቱ ሌሎች ጨዋታዎች አስቶንቪላ ኖቲንግሃም ፎረስትን 4 ለ 2፣ ክሪስታል ፓላስ በርንሌይን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
ኤቨርተንና ብራይተን ሆቭ አልቢዮንን 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
የሊጉ ጨዋታዎች ዛሬ እሁድ እና ነገ ቀጥለው የሚከናወኑ ይሆናል።
ዛሬ ዎልቭስ ሼፊልድን በሜዳው ሲያስተናግድ ነገ ደግሞ ዌስት ሃም እና ብሬንትፎርድ ይጫወታሉ።
ሊቨርፑል እና ቼልሲ ደግሞ በካራባኦ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታቸውን ዛሬ እሁድ ያደርጋሉ።












