የጠፉት ሩሲያዊ ጄነራል በሞስኮ ‘ታዩ ‘

ጄነራል ሰርጌይ ሱሮቪኪን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) ያልተሳካ ዓመጽ ካስነሳ በኋላ ከዕይታ ጠፍተው የነበሩት ሩሲያዊው ጄነራል ሞስኮ መሆናቸውን የሚያሳይ ፎቶ ወጣ።

ጄነራል ሰርጌይ ሱሮቪኪን የቫግነር ኃላፊ ከነበረው እና በቅርቡ በአውሮፕላን አደጋ ህይወቱ ካለፈው ዬቭጌኒ ፕሪጎዢን ጋር ቅርበት እንደነበራቸውም ተነግሯል።

ጄነራሉ በከሸፈው ዓመጽ ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል እየተመረመሩም እንደነበር ዘገባዎች ወጥተዋል።

ነገር ግን በዩክሬን የሚገኘው የሩሲያ ጦር የቀድሞ አዛዥ በሞስኮ የሚያሳይ ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተጋርተዋል።

“ጄኔራል ሰርጌይ ሱሮቭኪን ወጥቷል። በህይወት፣ ጤናማ በሆነ መልኩ ከቤተሰባቸው ጋር በሞስኮ መሆናቸውን ዛሬ የተነሳ ፎቶግራፍ አሳይቷል” ሲል የሩሲያው ታዋቂ ጋዜጠኛ ክሰኒያ ሾባክ በቴሌግራም ገጹ ላይ ፎቶውን በማያያዝ ጽፏል።

በፎቶው ላይ የጸሃይ መነጽር ያጠለቀ ግለሰብ ባለ ቀይ ጸጉር ሴት ጋር ሲራመድ ያሳያል። ግለሰቧ የጄነራሉን ሚስት አናን ብትመስልም ቢቢሲ የፎቶውን ትክክለኛነት አላረጋገጠም።

“ጄነራል ሱሮቪኪን ከቤተሰባቸው ጋር በመኖሪያ ቤታቸው ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት በእረፍት ላይ ናቸው እናም መከላከያም ሚኒስቴርም እያገኛቸው ነው” በማለት ሌላኛው ሩሲያዊው ጋዜጠኛ አሌክሲ ቬኔዲክቶቭ በቴሌግራም ገጹ ላይ አስፍሯል።

የቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) ተዋጊዎች ከወራት በፊት አመጽ አስነስተው የነበረ ሲሆን ወደ ሞስኮ እንዘምታለን ሲሉም አስፈራርተው ነበር።

በቅርቡም በሞስኮ አቅራቢያ በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ ፕሪጎዢን ጨምሮ ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።

የነሱም ሞት በርካታ መላምቶች እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኗል። የከሸፈውን አመጽ ተከትሎ የቫግነሩ መሪ በሞት ጥላ ስር እንደነበርም ሲገለጽ ቆይቷል።

ጄኔራል ሱሮቪኪን ለመጨረሻ ጊዜ በቪዲዮ የታየው የቫግነር ተዋጊዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ባሳሰቡበት መልዕክታቸው ነው።

ግለሰቡ ከቀናት በኋላ እንደታሰሩ መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቡም የት እንደነበሩ ግን የተረጋገጠ ነገር አልነበረም።

በዩክሬን የነበረው የሩሲያ ጦርን እንዲመሩ የተደረጉት ጄነራሉ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ከወራት በኋላ ነው።

ሩሲያ በሶሪያ በደረገችው ዘመቻ በጭካኔው ዝናን ያተረፉት ግለሰብ “ጄነራል አርማጌዶን” የሚል ቅጽል ስምም እንዲሰጣቸው ምክንያት ሆኗል።