በኪዬቭ ኃይል ከተቋረጠ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

ታትሟል

የኪዬቭ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ ከተቋረጠ ከተማዋን ለቀው ለመውጣት እንዲዘጋጁ ከንቲባው ቪታሊ ክሊሽኮ መመሪያ አስተላለፉ።

የሩሲያ ጥቃት ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረጉን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናዊያን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት አልቻሉም።

የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለመቋቋም እና ጥገና ለማከናወን መብራት በፈረቃ መሰጠት ተጀምሯል።

ሩሲያ በኃይል ማመንጫዎች ወይም ማስተላለፊያዎች ላይ ባደረሰችው ጥቃት 40 በመቶው የዩክሬን ኃይል ጉዳት ደርሶበታል ወይም ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው ሩሲያ “በመሠረተ ልማቶቻችን በተለይም በኃይል ማመንጫችን ላይ ትኩረት በማድረግ ጥቃት እየፈጸመች ነው” ብለዋል።

የጄኔቫ ኮንቬንሽን በጦርነት ወቅት “በሲቪል ንብረቶች ላይ” ጥቃት መፈጸም እንደማይገባ ይደነግጋል።

በዩክሬን ቴሌቭዢን ላይ የቀረቡት ከንቲባው ክሊሽኮ ሩሲያ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረጓን “ሽብርተኝነት” እና “የዘር ማጥፋት” ሲሉ ገልጸውታል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “እኛ ዩክሬናዊያንን አይፈልግንም። እሱ ግዛት ነው የሚፈልገው። እኛ የሌለንበትን ዩክሬንን ነው የሚፈልገው” ሲሉ የቀድሞው ቦክሰኛ ተናግረዋል።

“ለዚህ ነው የሚፈጸመው ነገር ሁሉ የዘር ማጥፋት የሆነው። ዓላማው እንድንሞት፣ እንዲበርደን ወይንም መኖሪያችንን እንድንለቅ እና ለመቆጣጠር ነው የሚፈልገው።”

በኪዬቭ መብራት ሙሉ ለሙሉ ከተቋረጠ የመጠጥ እና የፍሳሽ አገልግሎት ሊቋረጥ እንደሚችል ሌላ ባለስልጣን ተናግረዋል።

በክረምት ወራት የኪዬቭ ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች ሲሆን ምሽት ላይ ደግሞ ቅዝቃዜው ይጨምራል።

ከሊሽኮ ባለስልጣንት “የተቻላቸውን ሁሉ” በማድረግ ውሃ እና መብራት እንዲኖር ቢሞክሩም የሚመጣው ስለማይታወቅ ሌሎች አማራጮችንም እያዩ ነው።

መብራት እና ውሃ ባላቸው አካባቢዎች ሰዎች ጋር አብረው እንዲሆኑ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ የኪዬቭ ነዋሪዎችን ጠይቀዋል።

ባለስልጣናት ነዳጅ፣ ምግብ እና ውሃ በማጠራቀም ላይ ሲሆኑ ነዋሪውም ተመሳሳይ ሥራ እንዲከውን ጠይቀዋል። አንድ ሺህ የሚጠጉ የማሞቂያ ስፍራዎች ለድንገተኛ ጊዜ በሚል መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።