ትራምፕ የካፒቶል ሂል አመጽን እንዲያወግዙ ቢጠየቁም ፍቃደኛ አልነበሩም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አመጸኞች ካፒቶል ሂልን በኃይል ጥሰው ሲገቡ እርምጃውን ከማውገዝ ይልቅ ክስተቱን ዋይት ሃውስ ሆነው በቴሌቪዥን መስኮት መከታተልን መርጠዋል ተባለ።
ሪፓብሊካኑ አደም ኪንዚንግለር፤ ትራምፕ አመጸኞቹን እንዲያወግዙ ልጆቻቸው እና አማካሪዎቻቸው “ቢለምኗቸውም” ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ሲሉ ክስተቱን እየመረመረ ላለው ኮሚቴ ተናግረዋል።
“ምንም አይነት እርምጃን አለመውሰድን መርጠዋል” ሲሉ የሪፓብሊካን ፓርቲ አባሉ ኪንዚንግለር በዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ለሚመራው ኮሚቴ ተናግረዋል።
የካፒቶል ሂል አመጽን እየመረመረ የሚገኘው ኮሚቴ ትራምፕ ሁከቱን ለማስቆም ለሕግ አስከባሪ አባላትም ይሁን ለብሔራዊ ደኅንነት አማካሪዎቻቸው ስልክ እንዳልደወሉ ተነግሮታል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዋይት ሃውስ ባለው መመገቢያ ክፍል ከ2 ሰዓት በላይ የዘለወቀውን የፎክስ ኒውስ ዘገባ ሲከታተሉ ነበር ተብሏል።
የቨርጂኒያው ዴሞክራት ፓርቲ አባል ኤልይን ሉሪያ፤ “የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪዎች እና የቤተሰብ አባላት ከየትኛውም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሚጠበቀውን እንዲያደርጉ ቢለምኗቸውም ትራምፕ መመገቢያ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ጥቃቱ ሲፈጸም በቴሌቪዥን መስኮት ሲከታተሉ ነበር” ብለዋል።
ትራምፕ አመጹን ለማስቆም እርምጃ ከመውሰድ የተቆጠቡት “በስልጣን ላይ ለመቆየት ያላቸውን የግል ፍላጎት” ለማሳካት ነው ተብሏል።
ትናንት ሐሙስ ሐምሌ 14/2014 ዓ.ም. በአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ ከአንድ ዓመት በፊት የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሂልን በኃይል ሲወሩ በነበሩት 187 ደቂቃዎች ዶናልድ ትራምፕ ምን ሲያከናውኑ ነበር የሚለውን ለመለየት ለ8ኛ ጊዜ ምስክሮችን ሰምቷል።
ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት በአሜሪካ የተደረገውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደን ማሸነፋቸውን ተከትሎ የሕዝብ እንደራሴዎች የባይደንን የምርጫ ውጤት ለማረጋገጥ ስበሰባ ላይ ሳሉ፤ የትራምፕ ደጋፊዎች ወደ ሕንጻው በኃይል በመግባት የሕዝብ እንደራሴዎችን ስብሰባ አውከዋል።
ትራምፕ ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ በአውሮፓውያኑ 2020 የተካሄደው ምርጫ የተጭበረበረ ነው በማለት ሽንፈታቸውን አልተቀበሉም።
ይህ በአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ፤ ሪፐብሊካኑ ትራምፕ፤ በዴሞክራቱ ጆ ባይደን የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመቀልበስ ሕጋዊ ያልሆኑ እርምጃዎችን ወስደዋል የሚል ክስ ለመመስረት የሚያስችለውን መረጃ እያስባሰበ ነው።
በቀጣይ 2024 በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ ያመላከቱት ትራምፕ፤ ጉዳያቸውን እየመረመረ የሚገኘውን ኮሚቴ አጥብቀው ይተቻሉ።
ትራምፕን እየመረመረ የሚገኘው ኮሚቴ እስካሁን የተቀበላቸውን ምስክርነቶች ይዞ ትራምፕ ላይ ‘የኮንግረሱን ይፋዊ ሥራ ማደናቀፍ’ እና ‘የአሜሪካን ሕዝብ ለማጭበርበር ማሴር’ የሚሉ ክሶችን መመስረት ይቻላል ሲል ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።












