ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ - ማን ያሸንፋል? የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

በ20ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሊቨርፑል ማንቸስተር ዩናይትድን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
"የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ከሆኑ ሽንፈቱ አነስተኛ እንዲሆን ነው ምኞታቸው" ሲል የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን ስለጨዋታው ገልጿል።
"ከዚህ ጨዋታ ነጥብ እናገኛለን ብሎ የሚያስብ አንድም የዩናይትድ ደጋፊ አይኖርም። የሚጠበቀው ሊቨርፑል በምን ያህል ጎል ያሸንፋል የሚለውን ነው" ሲል አክሏል።
ሱተን ይህንን ጨዋታ ጨምሮ ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ የሚከናወኑትን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ገምቷል።
ቅዳሜ
ቶተንሃም ከኒውካስል
ኒውካስል ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች በማሸነፍ 16 ጎሎችን አስቆጥሮ አንድ ጎል ብቻ አስታግዷል።
ቶተንሃም በተቃራኒው በውጤት መሽቆልቆል ውስጥ ይገኛል።
በዚህ ጨዋታ ጎል ማስቆጠር ቢችልም ኒውካስል ግን ሦስት ነጠብ ያገኛል።
ግምት፡ 1 – 2
በርንመዝ ከኤቨርተን
ጎል የማስቆጠር ችግር ያለበት ኤቨርተን ዘንድሮ 15 ጎሎችን ብቻ ነው ማስቆጠር የቻለው።
ሁለቱ ቡድኖች ነሐሴ ላይ ተገናኝተው ኤቨርተን 2 ለምንም ቢመራም በርንመዝ 3 ለ 2 ማሸነፍ ችሏል።
በርንመዞች ዕድሎችን መፍጠር መቻላቸውን ደጋግመው በማሳየታቸው በዚህ ጨዋታ አሸናፊ ሆነው ይወጣሉ።
ግምት፡ 1 – 0
አስቶን ቪላ ከሌስተር
አስቶን ቪላ በቅጣት ምክንያት ጆን ዱራንን እና ሞርጋን ሮጀርስን ቢያጣን ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ማግኘት ይችላል።
ቪላ በሜዳው ጠንካራ ሲሆን ሌስተር ደግሞ ከሜዳው ውጭ ደካማ መሆኑ ተደጋግሞ ታይቷል።
ሌስተር ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረው ጨዋታ ጥሩ ቢንቀሳቀስም ተሸንፎ ወጥቷል።
በዚህ ጨዋታም ቪላ ያሸንፋል።
ግምት፡2 – 0
ክሪስታል ፓላስ ከቼልሲ
ቼልሲ በተከታታይ ውጤት ማግኘት ካለመቻሉም በላይ በኢፕስዊች ሲሸነፍ ጥሩ መንቀሳቀሰም አልቻለም።
ክሪስታል ፓላስ ደግሞ ባለፉት 11 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ነው የተሸነፈው።
ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስላል።
ግምት፡ 1 – 1

ማንቸስተር ሲቲ ከዌስት ሃም
ለዌስት ሃም የውድድር ዓመቱ ኮከብ የነበረው ጃሮድ ቦዌን መጎዳት ለቡድኑ ትልቅ ኪሳራ ነው።
ለሲቲ ደግሞ ከሌስትር ድል በኋላ በውጤታማነት ለመቀጠል ጥሩ ዕድል የሚፈጥር ነው።
ሲቲ በጥሩ ብቃት ባያሸንፍም አሁን የሚያስፈልገው እያሸነፈ ወደ ጥሩ አቋሙ ቀስ በቀስ መመለስን ነው።
በዚህ ጨዋታ ሲቲ ጥሩ መንቀሳቀስ ባይችልም ሦስት ነጥቡን ግን ያሳካል።
ግምት፡ 2 – 0
ሳውዝአምፕተን ከብሬንትፎርድ
ሁለቱም ቡድኖች በጥሩ አቋም ላይ ካለመሆናቸው አንጻር ይህንን ጨዋታ መገመት ከባድ ይሆናል።
ቅዱሳኑ በአዲሱ አሰልጣኝ ኢቫን ዩሪች ስር ውጤታማ ለመሆን ቢሞክሩም ነጥቦችን ለመሰብሰብ ግን በድጋሚ የሚቸገሩ ይመስላል።
ብሬንትፎርድ በተቃራኒው ሊጉን የተላመደ እና ጎሎችን ማስቆጠር ሚችል ቡድን ነው።
ግምት፡ 1 – 2

ብራይተን ከአርሰናል
መድፈኞቹ ያለቡካዮ ሳካ፣ ካይ ሃቨርትዝ እና ዴክላን ራይስ በቀላሉ ብሬንትፎርድን ማሸነፍ ችለዋል።
በዚህ ጨዋታ አርሰናል ማሸነፍ ስለሚፈልግ እና ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች በአምሰቱ አቻ ወጥተው በሁለቱ የተሸነፉት ብራይተኖች ለሦስት ነጥቡ ስለሚጫወቱ ቀላል ጨዋታ አይሆንላቸውም።
የማይክል አርቴታ ቡድን ግን ጨዋታውን በበላይነት የማጠናቀቅ አቅም አለው።
ግምት፡ 1 – 2
እሑድ
ፉልሃም ከኢፕስዊች
ኢፕስዊች በሊጉ ለመቆየት በሚቻለው ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።
ሆኖም ግን በሜዳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ቼልሲን በማሸነፍ ሦስት ነጥብ ቢያሳኩም በዚህ ጨዋታ ግን ውጤታማ መሆን አይችሉም።
ፉልሃም ባለፈው ሳምንት ነጥብ ቢጥልም በሜዳው ግን ጠንካራ መሆኑን ደጋግሞ አስመስከሯል።
አንቶኒ ሮቢንሰን እና የአሌክስ ዒኦቢ ጥምረት ቡድኑን ለድል ያበቃዋል።
ግምት፡ 1 – 0

ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ
ሁሉቱ ቡድኖች ታሪካዊ ተቀናቃኝ ቢሆኑም በወቅታዊ አቋማቸው ግን በተለያየ ጫፍ ላይ ተቀምጠዋል።
ማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ከሊጉ ስለመውረድ ለምን እንዳወረ መገመት ቀላል ነው።
ኦልትራፎርድ ላይ ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በኒውካስል የደረሰበት ስንፈትን ለተመለከተ በአንፊልድስ ምን የተለየ ነገር ይጠበቃል ብሎ ይጠይቃል።
ሊቨርፑል ጎሎችን ማስቆጠር እንደሚችል ደጋግሞ አስመስክሯል።
ሊቨርፑል ጨዋታውን ማሸነፉ ቢጠበቅም ዋናው ጥያቄ ስንት ጎሎችን አስቆጥሮ የሚለው ነው።
ዩናይትድ ለክብሩ፣ ለማልያው እና ለአርማው ሲል እንደሚጫወት ቢጠበቅም ይህም ምንም ለውጥ አያመጣም።
ሊቨርፑል ካለበት አቋም አንጻር ሩበን አሞሪም በዚህ ጨዋታም ይሸነፋሉ።
ግምት፡ 5 – 0
ሰኞ
ዎልቭስ ከኖቲንግሃም ፎረስት
በኖቲንግሃም ድንቅ ሥራ እየከወኑ የሚገኙት ኑኖ እስፕሪንቶ ሳንቶ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ዎልቭስ የሚመለሱበት ጨዋታ ነው።
ዎልቭስ ጥሩ መንቀሳቀስ ቢጀምርም የአጥቂው ሉካስ ኩኛ በቅጣት አለመሰለፍ ቡድኑን ይጎዳዋል።
ፎረስት በዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥቦችን ያሳካል።
ግምት፡ 0 – 1












