በዓለም ዋንጫ አስሩ ምርጥ የብሔራዊ ቡድኖች ማሊያዎች የትኞቹ ናቸው? ዝነኛ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

አንዳንዶች የኖርነውን ሕይወት በዓለም ዋንጫዎች መለካት ይቻላል ይላሉ። በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከልጅነት እስከ ወጣትነት ከዚያም በላይ ያለውን ዕድሜያችንን ነክቶታል።
ወደ ኋላ መለስ ስንል የምንወደው ቡድን፣ የምንዘምርላቸው ጀግና ተጨዋቾች፣ የሚለብሱት ዝነኛ ማሊያዎች ይታወሱናል።
ዛሬ እነዚህን ታሪካዊ እና ዘመን የማይሽራቸው ማሊያዎችን እንመለከታለን።
ለመሆኑ እነዚህን ማሊያዎች እስካሁን ድረስ የምናስታውሳቸው ለምንድን ነው? ዝነኛ ያደረጋቸውስ ምንድን ነው?
ማቲው ዎልፍ በአውሮፓውያኑ 2018 ለተካሄደው የዓለም ዋንጫ ለናይጄሪያ ቡድን እንዲሁም ለአሸናፊው የፈረንሳይ ቡድን ማሊያ ዲዛይን በማድረግ በስፋት ይታወቃል።
የዲዛይነሩ ሥራዎች ለፈረንሳይ እግር ኳስ ክለብ - ፒኤስጂ እንዲሁም ከመሥራቾቹ አንዱ የሆነበት የዩናይትድ እግር ኳስ ሊግ ክለብ- ቬርሞንት ግሪን ቡድን ትጥቆችን ያካትታሉ።
ስለ የእግር ኳስ ትጥቆችም ጠንቅቆ ያውቃል።
ዎልፍ "በጣም የምወደው የእግር ኳስ ትጥቅ በልጅነቴ በ1990ዎቹ እና በ2000 መጀመሪያዎች የነበሩት ናቸው" ይላል።
"እነዚህ ጊዜያት ተጨዋቾቹ እውነተኛ ጀግኖች፤ ትጥቃቸው ምትሃታዊ መስሎ ይሰማኝ የነበረበት የሕይወት ምዕራፍ ነው።"
"በአውሮፓውያኑ 1998 ሜክሲኮ፣ በ1994 አሜሪካ፣ በ1990 እና በ1994 ጀርመን፣ በ1998 ጃፓን፣ ከ2002 ወዲህ ደግሞ የናይኪ ማሊያዎች፣ እንዲሁም በ2002ቱ የካሜሩን እጅጌ የሌለው ማሊያ በአዕምሮዬ ተስለው የቀሩ የተለዩ ትጥቆች ናቸው። እንደ ታዳጊ ጥሩ እና በጣም ቆንጆ እንደሆኑ ነበር የሚሰማኝ" ብሏል።
"በተለይ ቲሸርታቸው ዝነኛ ነበር። ምክንያቱም የሆነ ሰው ሲለብሰው የሚታየው በአግራሞት ነበር። ጊዜው የእግር ኳስ ትጥቆችን የምንመለከትበት እና የምናደንቅበትን መንገድም ቀይሮታል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዎልፍ አሁን ላይ "ዝነኛ" የሆነ ማሊያ ማግኘት ከባድ እንደሆነ ያምናል። "ሁኔታው ተቀይሯል፤ የዓለም ገበያም የተጨናነቀ ነው" ይላል ምክንያቱን ሲያስረዳ።
"አሁን ላይ ብዙ ቡድኖች እንዲሁም የክለቦችም ሆኑ የአገራት ብዙ አዳዲስ ትጥቆች አሉ። በዚህ ሁሉ ውስጥ አንድ ማሊያ ነጥሮ መውጣት ከባድ ነው።"
"የየአገራትን ፈጠራ እና በመለያቸው ላይ ባህል ተወክሎ ማየት የሚያበረታታ ቢሆንም፤ የትኛው በትክክል የአገሩን ባህል ወክሏል የሚለው እና የአገልግሎት ጊዜ በተጠቃሚዎች ጥያቄ ይነሳበታል" ሲልም አክሏል።
10 ዝነኛ የዓለም ዋንጫ ማሊያዎች
የዎልፍን ሃሳብ እዚህ ላይ ገታ አድርገን በትዝታ ወደ ኋላ የሚመልሱንን ትጥቆች እንመልከት።
ትውስታዎቹ በ1990ዎቹ እና በ2000 መጀመሪያ ላይ ወደነበሩት ደማቅ ቀለም ያላቸውና ሰፋፊ ማሊያዎች እንዲሁም በ1980ዎቹ ወደነበሩት እና አሁን ላይ ፋሽን ሆነው ወደመጡት ትጥቆች ይወስዱናል።
ለመሆኑ እናንተ የምትወዱትና የማትረሱት ማሊያ የትኛው ነበር? ቢቢሲ 10 ዝነኛ የዓለም ዋንጫ ማሊያዎችን በደረጃ አስቀምጧል።
10. በ2002 የካሜሩን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህ የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ትጥቅ የተሠራው ለዓለም ዋንጫ ጨዋታ አልነበረም። ሆኖም በዓለም እግር ኳስ ታሪክ የማይረሳ ማሊያ ሆኗል።
ቡድኑ ይህን እጅጌ የሌለው ማሊያ ለብሶ የተጫወተው በ2002ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።
በጨዋታው በፍጹም ቅጣት ምት ሴኔጋልን 3 ለ2 በሆነ ውጤት በመርታት ዋንጫ አንስቷል።
እጅጌ አልባ ማሊያቸው ቀልብ የሳበውም ያኔ ነበር።
የቀድሞው የቡድኑ መሃል ተጨዋች ኤሪክ ጄምባ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ሲናገር "በአፍሪካ ሁሉም ሰው ይህንን ማሊያ መልበስ ይፈልግ ነበር" ብሏል።
አሜሪካዊቷ ቴኒስ ተጨዋች ሴሪና ዊሊያምስ ሳትቀር በዚያው ዓመት በፈረንሳይ በተካሄደው የቴኒስ ውድድር ላይ በካሜሩን ቡድን ማሊያ መነሻነት የተሠራ ትጥቅ ለብሳ ተጫውታለች።
ሆኖም ቡድኑ ማሊያውን በዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ እንዳይለብስ በዓለም እግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) ታግዷል። ይህም በወቅቱ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።
ፊፋ "ይህ ቲሸርት ሳይሆን ሰደርያ ነው፤ ሕገ ወጥ ነው" ሲል ነበር ዕገዳ የጣለበት።
በጃፓን እና በደቡብ ኮሪያ ለተካሄደው የዓለም ዋንጫም በማሊያው ላይ እጅጌ እንዲጨምር ለአልባሳት አምራቹ ፑማ ተነግሮት አጭር እጅጌ ተጨምሮበታል።
የካሜሩን ትጥቅ የፊፋ ኃላፊዎችን ሲያስቆጣ ይህ የመጨረሻው አይደለም። ከሁለት ዓመት በኋላም ቲሸርቱ እና ቁምጣው ተያይዞ የተሰፋ ሙሉ ትጥቅ በእግር ኳስ ባለሥልጣኑ ታግዶ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
9. በ1966 እንግሊዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህንን ማሊያ በእንግሊዝ በበጋ ወቅት በምግብ ቤቶች እና መዝናኛ ቦታዎች ማየት የተለመደ ነው።
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የሚለብሰው የኩራት እና የፅናት ምልክት የሆኑት ሦስቱ አንበሶች ያሉበት ቀይ ማሊያ ይወደዳል። ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቱ ብቸኛ የዓለም ዋንጫ ድል የተመዘገበበት በመሆኑ ነው።
ለንደን በሚገኘው ዌምብሊ ስታዲየም እንግሊዝ ከምዕራብ ጀርመን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጂኦፍ ኸርስትስ የሠራው ሃትሪክ እና ኳሷ መስመሩን አልፋ ከመረቧ ጋር ሲገናኙ የነበረው ስሜት የሚረሳ አይደለም።
በጨዋታው እንግሊዝ ምዕራብ ጀርመንን 4 ለ2 በሆነ ውጤት ነበር ያሸነፈችው።
የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ቦቢ ሞር ከቡድን አባላቶቹ ጋር ዋንጫውን ያነሳበትን ሁነትም ያስታውሳል።
በ1982 እና በ1990 የዓለም ዋንጫዎች ብሔራዊ ቡድኑ የለበሳቸው የተለያዩ ማሊያዎች ተወዳጅ ቢሆኑም አንድ የእንግሊዝ ማሊያ ብቻ መኖር ካለበት ቀዩን ማሊያ የሚተካው አይኖርም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
8. በ1982 ፈረንሳይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ይህ የእኔ በጣም ገራሚ ጨዋታ ነበር። በወቅቱ የነበረውን ስሜት እና ሁኔታ ፊልምም ሆነ ሌላ ጨዋታ እንደገና ሊያመጣው አይችልም፤ ሙሉ ነበር፤ አስደናቂም ነበር" ብሏል የፈረንሳዩ አምበል ሚሸል ፓላቲኒ በ1982 ብሔራዊ ቡድኑ - ለስ ብሉስ - በግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በምዕራብ ጀርመን ሲሸነፍ በሰጠው አስተያየት።
የጀርመኑ ግብ ጠባቂ ሃራልድ ሹማቸር ከፈረንሳዩ ተከላካይ ፓትሪክ ባቲስተን ጋር የተጋጩበት አስደንጋጭ ክስተት የታየበትም ነበር። ባቲስተን በዚህ አደጋ ጥርሱን አጥቶ እንደነበር ተነግሯል።
በስፔን ስቪሌ በተካሄደው ጨዋታ ፈረንሳይ በተጨማሪ ሰዓት መሪነቷን ተነጥቃ 3 ለ3 አቻ የወጣች ሲሆን፣ በቅጣት ምት በዌስት ጀርመን 5 ለ 4 ተረታለች።
ፈረንሳይ በስቪሌ ከፍተኛ ሙቀት የተረጋጋች ትመስል ነበር። ትጥቃቸውም ፈረንሳዮች ያንን ሁሉ ለመቋቋም ያደረጉት ጥረት ምልክት ሆኗል።
7. በ1974 ኔዘርላንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አመጸኛው፣ ግትሩ እና በራስ መተመማን ያለው ጆሃን ክራይፍ የኔዘርላንድ አጠቃላይ እግር ኳስ አብዮት ምልክት ነው።
ክራይፍ ከአያክስ ቡድን አባላት ጋር ሦስት የአውሮፓ ዋንጫዎችን ያሸነፈ ሲሆን፣ ለ1974ቱ የዓለም ዋንጫ ሲያልፍ ሁለት ጊዜ የባሎን ዶር ሽልማትን ወስዷል። ይህ በጣም የሚታወስ አጋጣሚ ነው።
ክራይፍ ይበልጥ ዝነኛ የሆነው በጀርመኑ ዶርትሙንድስ ስታዲየም በተካሄደ ጨዋታ ኔዘርላንድ በስዊድን ላይ አብላጫ ስትይዝ ነበር።
ባለ ረዥም ፀጉሩ የቡድኑ መሪ ለአባላቱ ያስታጠቀው የተለየ እና በእጅጌያቸው ላይ የአዲዳስ መለያ የሆኑ ሦስት መስመሮች ያሉት ትጥቅ ነበር።
ሆኖም ክራይፍ ከፑማ ጋር የግል ውል ስለነበረው የአዲዳስን ማሊያ ለመልበስ ፈቃደኛ አልነበረም።
በብራንዱ በተጨዋቾች እና በሆላንድ የስፖርት ባለሥልጣናት መካከል ውዝግብ ከተነሳ በኋላ ማሊያው ላይ ያሉት መስመሮች እንዲነሱ ተደርገዋል።
"የኔዘርላንድ የእግር ኳስ ማኅበር ለተጨዋቾቹ ሳያሳውቅ ከአዲዳስ ጋር ኮንትራት ተፈራርሟል" ብሏል ክራይፍ በግለ ታሪኩ ላይ። "ማሊያው የእነርሱ ስለነበር መናገራቸው እንደማያስፈልግ ነበር ያሰቡት፤ ግን የማጠልቀው እኔ እንደሆንኩ ነገርኳቸው" ብሏል።
6. በ1998 ክሮሽያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ1998 በፈረንሳይ አስተናጋጅነት በተካሄደው የዓለም ዋንጫ የክሮሺያ ቡድን ዐይን የሚስብ ማሊያ ነበር የለበሱት።
የቡድኑ ተጨዋች ዳቮር ሱከር በሽንጡ በኩል ቀይ እና ነጭ ስኩዌር ያለው ሰማያዊ ማሊያ ለብሶ ሲታይ ያስደምም ነበር።
ዲዛይኑ የክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን መለያ የሆነ ሲሆን፣ በእግር ኳስ ጨዋታዎች በቀላሉ እንዲለዩም አድርጓቸዋል።
ክሮሺያ ቀደም ብሎ በዩሮ 96 ጨዋታ አስገራሚ ብቃቷን አሳይታ ነበር። እዚያም ቡድኑ ትኩረት የሚስብ የስፖርት ትጥቅ ለብሶ ነበር።
የዓለም ዋንጫው ግን በአገሪቷ ታሪክ የተለየ የስፖርት አጋጣሚ ስለነበር ማሊያው ከአእምሮ አይጠፋም።
ክሮሺያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ የተሳተፈችው ነጻነቷን ካወጀች ከሰባት ዓመታት በኋላ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
5. በ2018 ናይጄሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያ ቡድን በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ የለበሰው ማሊያ ትልቅ ክስተት ነበር። ብዙም ያልተለመደ፣ ከባህል እና ፋሽን ጋር የተዛመደ በመሆኑ ነበር ዝነኛ የሆነው።
ማሊያው ይፋ ከሆነ በኋላ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ለመግዛት ያዘዙት ሲሆን፣ ነጋዴዎች ለንደን በሚገኘው የናይኪ ማከፋፈያ ተሰልፈው ታይተዋል።
ማሊያውን ዲዛይን ያደረገው ዲዛነይር ዎልፍ "ከናይጄሪያ የስፖርት ትጥቅ ታሪክ በቀጥታ የወሰድነው ነው " ብሏል።
"በ2002 የነበረው ማሊያ መነሻ ነበር። ያን ደስ የሚለውን ደብዛዛ አረንጓዴ ማሊያ መልሼ ማምጣት ፈልጌ ነበር። ከ1994 - 95 ከነበሩት ትጥቆችም መነሻ ሃሳብ ወስደናል" ሲል አስረድቷል።
"ዓላማችን አዲስ ነገር መፍጠር አልነበረም። አገሪቱ ያላትን የእግር ኳስ ማንነት ማምጣት ነበር።"
"በብዙ መልኩ ጊዜው በጣም ጥሩ ነበር። ናይጄሪያ ዓለም አቀፍ ፋሽን፣ ሙዚቃ፣ ግጥም፣ ጥበብ፣ ፊልም ወዘተ ኢንደስትሪ እየገባች ነበር። የስፖርት ትጥቁ የመጣውም በዚህ መሃል ነው። ሕዝቡም በቀላሉ የተቀበለው በዚህ መነቃቃት ውስጥ ስለነበረ ነው ብዬ አስባለሁ።"
"እውቅናው ሁሉንም አንድ ላይ ያሰናሰሉት የናይኪ ቡድን ነው። ትጥቁ በአንድ ዲዛይነር ምክንያት አይደለም ክስተት የሆነው። ዝነኛ የሆነው በእያንዳንዱ ሥራ ብዙ ሰዎች ሃሳብ ስላዋጡ ነው" ብሏል።
4. በ1970 ብራዚል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሚያከራክር ቢሆንም በዓለም ዋንጫ ከብራዚል ቡድን ጋር የሚመሳሰል ቀለም ያለው ማሊያ ያለው አገር የለም።
ምንም እንኳን ምሥሎቹ የደበዘዙ ቢሆኑም በ1970 የለበሱት ቢጫ ቀለም ያለው ትጥቅ በጣም ያማረ እና ትኩረት የሚስብ ነበር። ትጥቁ በሜክሲኮዋ ፀሐይ የዓለም ኮከብ ተጨዋቾች ላይ ልክክ ብሎ ይታይ ነበር።
ፔሌ፣ ካርሎ አልቤርቶ፣ ሪቬሊኖ፣ ጀርዚንሆ ማሊያውን ለብሰው የሚያሳየው ቪዲዮ በየዓለም ዋንጫዎቹ ማስታወቂያዎች በስፋት የሚዘዋወር ምሥል ሲሆን፣ ብራዚሎች ጣሊያንን ሲረቱ የነበረውን ጨዋታ ያስታውሳል።
በዚህም ምክንያት በእግር ኳሱ ዓለም ቢጫው እና ቀለል ያለው ማሊያ ዝነኛ ሆኗል።
3. በ1994 አሜሪካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፊፋ የ1994ቱን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አሜሪካ እንደምታዘጋጅ ሲያስታውቅ ከአገሪቷ ውጪ ባሉት አብዛኛው የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ ጥርጣሬ እንደነበር የቀድሞው የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አላን ሮተንበርግ ያስታውሳሉ።
"ይህች እግር ኳስ ተጨዋች ያልሆነች አገር እንዴት ይህንን ማሊያ ልትለብስ ቻለች ? ያሉም ነበሩ" ይላሉ።
በወቅቱ ከአሜሪካ ክለቦች ይልቅ ከአሜሪካ ሴንትራል ጋር ውል የነበራቸው ተጨዋቾች መሳቂያ መሆን አይፈልጉም ነበር።
ሆኖም አዲዳስ ለጨዋታው ማሊያውን ይፋ ሲያደርግ አሌክሲ ላላስ እና ቡድኑ ማመን ነበር ያቃታቸው።
በጣም ሰፊ እና የተለጠጡ ከዋክብት በውሃ ሰማያዊ መደብ ላይ የሚታዩበት ማሊያ የአሜሪካ እንደሆነ ጥርጥር አልነበረም።
በጣም ደማቅ ነበር፤ የቡድኑ አባላት እንዳይቀለድባቸውም ፈርተው ነበር።
ሆኖም በተጨዋቾቹም ሆነ በደጋፊዎቹ በጣም ዝነኛ እና የሚወደድ ሆነ። በጨዋታው ላይ አሜሪካ ያሳየችው ብቃትም ለዚህ አስተዋፅኦ ማድረጉ የማይካድ ነው። ሆኖም በመጨረሻዎቹ 16ቱ ምድብ በብራዚል 1 ለ 0 ተሸንፋ ከውድድር ውጪ ሆናለች።
ይህ ማሊያ በተወዳጅነቱ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አሁን ላይ የዓለም ዋንጫ መልሶ ወደ አሜሪካ በመግባቱ ሊሆን ይችላል።
ቢሆንም የ1994ቱ የዓለም ዋንጫ በጉልህ የሚታወሱ ትጥቆች የታዩበት ጨዋታ ነበር።
2. በ1986 አርጀንቲና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ1986 አርጀንቲና ከእንግሊዝ ጋር ባደረገችው ጨዋታ የዓለምን ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ያሸነፈችባቸው ሁለት ታሪካዊ ግቦችን አይታለች።
አንደኛው 'የእግዜር እጅ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ዲያጎ ማራዶና ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ ስትሆን፣ ሌላኛዋ መሃል ሜዳ ላይ ኳሷን በመቆጣጠር እና አምስት የእንግሊዝ ተጨዋቾችን በማለፍ ያስቆጠራት አስደማሚ ግብ ነች።
ግን በዚያች አስደናቂ ዕለት ግቦቹ ብቻ ሳይሆኑ የአርጀንቲና ቡድን የለበሰው ማሊያም ዕኩል ይታወሳል።
ይህ ዝነኛ ማሊያ የተዘጋጀው በ24 ሰዓታት ውስጥ ነበር።
ፊፋ ቀደም ብሎ ከእንግሊዝ ነጭ ማሊያ ጋር እንዳይጋጭ በሚል ቡድኑ ጥቁር ሰማያዊ ማሊያውን መልበስ እንዳለበት ለአርጀንቲና አሳውቆ ነበር።
ሆኖም ቀደም ሲል ኡራጓይን ባሸነፉበት ጨዋታ ማሊያው ለሜክሲኮ ሙቀት በጣም ወፍራም ሆኖባቸው ስለነበር ያንን መልበስ አልቻሉም ነበር።
የፈረንሳይ ትጥቅ አምራቹ ሉ ኮክ ስፖርቲፍ በወቅቱ ሌላ አማራጭ አልነበረውም።
ከዚያም የአርጀንቲና ቡድን ሥራ አስኪያጅ ካርሎ ቢላርዶ ከሜክሲኮ ከተማ ውጪ ወደ ቴፒቶ ሠራተኞችን በመላክ አዲስ ማሊያ ለማዘጋጀት ልብስ አስገዛ።
የትጥቅ ባለሙያዎች አርጀንቲና እንግሊዝን ከመግጠሟ በፊት ማሊያዎቹን ከቁጥር እና ከብሔራዊ መለያ ጋር ለማስተካከል 24 ሰዓታት ወስዶባቸዋል።
አሁን ወደ ኋላ የመለሰንን የዚህን ማሊያ የመጨረሻውን ዲዛይን ያፀደቀውም ማራዶና ነበር።
ማራዶና ማሊያውን እንዳየው "ምን ዓይነት ደስ የሚል ቲሸርት ነው፣ ካርሎስ! በዚህ እንግሊዞችን እናሸንፋለን" ነበር ያለው።
የእንግሊዙ አማካይ ተጨዋች ስቲቭ ሆጅ የዚያን ዕለት ለማስታወሻ ከማራዶና ጋር የተቀያየረውን ይህን ማሊያ ከ36 ዓመታት በኋላ ለጨረታ አቅርቦት ነበር። ማሊያው በ7.1 ሚሊዮን ፓውንድ ተሸጧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
1. በ1990 ዌስት ጀርመን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቁጥር አንድ የተቀመጠው ዘመን አይሽሬ፣ ብዙ ተፈላጊ የሆነ እና አዲስ ለሚሠሩ ማሊያዎች ፈርቀዳጅ የሆነው በ1990 የዓለም ዋንጫ ዝነኛው የምዕራብ ጀርመን ቡድን የለበሰው ትጥቅ ነው።
'ኤ ካልቸር ኦፍ ኪትስ' ፀሐፊ የሆኑት ጆን ብሌር ለቢቢሲ ስፖርቲንግ ዊትነስ ፕሮግራም ሲናገሩ "ከዚያ በፊት ከነበሩት ጋር ስናወዳድራቸው ቲሸርቶቹ ወጥ እና ቀለል ያለ ዲዛይን ያላቸው ናቸው" ብለዋል።
"ዘመኑን የዋጀ፣ አሸናፊ ቡድን እና የመጀመሪያው እውነተኛ ገላጭ ዲዛይን የተጣመሩበት ነው።"
በእርግጥ ማሊያው ከዓለም ዋንጫ በፊት እየተተወ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የተለበሰው አዘጋጇ ምዕራብ ጀርመን በግማሽ ፍፃሜ ሽንፈትን ባስተናገደችበት በ1988 የአውሮፓ ዋንጫ ነበር።
ዲዛይነሯ ኢና ፍራንዝማንም ለዓለም ዋንጫ አዲስ ማሊያ እያዘጋጀች ነበር። ሆኖም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፍራንዝ ቤከንባወር ጣልቃ ገብቶ የቀድሞውን ማሊያ ይዘው እንደሚቀጥሉ ነግረዋታል።
ለአዲዳስ የቴኒስ ተጨዋቾች ልብስ የምትሠራው ፍራንዝማን የእግር ኳስ አድናቂ አልነበረችም። ግን በብሔራዊ ቡድኑ ማሊያ "ትንሽ አብዮት" ለመፍጠር ነበር የሠራችው።
"የአዲዳስ መሥራች አዶልፍ ልጅ ሆርስት ዳስለር ነበር ትንሽ ቀለም እንድንጠቀም ሃሳቡን ያመጣው፤ ያው ቀለሞቹ የጀርመን እንደሚሆኑ ይታወቅ ነበር" ብላለች።
ዳስለር በ1987 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ምዕራብ ጀርመን የዓለም ዋንጫን ስታነሳ እና በጣሊያን በተካሄደው የዓለም ዋንጫ የብዙዎችን ቀልብ ስትስብ ለመመልከት አልታደለም። ሆኖም ለፍራዝማን ከአስርተ ዓመታት በኋላም ቢሆን መደነቁ ጥሩ አጋጣሚ ነው።
"ማሊያው ከዓመታት በኋላ ልዩ ሥራ ሆኗል፤ ባለው ተወዳነጅትም እኮራለሁ። ሁሉም ሰው ከዚህ ጀርባ ያለውን ታሪክ ማወቅ ይፈልጋል" ብላለች።












