በጋዛ አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

ታትሟል

እስራኤል በጋዛ በወሰደቻቸው ወታደራዊ ዘመቻዎች አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑት ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

እነዚህ ግድያዎች አሁንም እንደቀጠሉ ሲሆን ባለፉት 24 ሰዓታት 178 ሰዎች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም እስካሁን ባለው የጦርነቱ ሂደት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከሞቱበት ቀናት አንዱ ያደርገዋል።

ጦርነቱ በቀጠለበት ወቅት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ፍልስጤም እንደ አገር የመቀበለን ሃሳብ በድጋሚ ውድቅ አድርገዋል።

ዋይት ሃውስ በበኩሉ የሁለት አገራት መፍትሄን በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል ነገሮችን “በተለያየ መንገድ እንደሚያዩ ግልጽ ነው” ብሏል።

እስራኤል በጋዛ ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው መስከረም 26 የሐማስ ተዋጊዎች በደቡብ እስራኤል 1ሺህ 300 ሰዎችን ገድለው ከ240 በላይ የሚሆኑትን ያገቱበትን ጥቃት ተከትሎ ነው።

ሐማስ ጥቃቱ እስራኤል የፍልስጤም ግዛቶችን መያዟን ለመቃወም እና የፍልስጤም እስረኞችን የሚፈቱበት “ትክክለኛ መንገድ” ነው ሲል ገልጾታል።

የእስራኤል የአየር እና የምድር ዘመቻ ትኩረት ያደረገው በደቡባዊ ጋዛ ላይ ሲሆን በዚህም የሐማስ ከፍተኛ አዛዦች ይገኙበታል በተባለበት የዃን ዩኒስ ላይ ያተኮረ ነው።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በአካባቢው 830 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ ማግኘቱን ገልጿል።

ጦሩ ይፋ ያደረገው ቪዲዮ በውስጡ ፍራሽ እና ክፍሎች ያሉት ዋሻ ያሳያል። ዋሻው ህጻናትን ጨምሮ ወደ 20 የሚጠጉ ታጋቾች እንደነበሩበት እስራኤል ግምት አላት። ዋሻው ሲገኝ ግን ማንም በውስጡ አልተገኘም።

የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል ሌላ ጥቃት ገጥሟቸዋል። እስራኤል ወታደሮቿን እና ታንኮቿን ወደ ደቡብ ስታንቀሳቅስ ሐማስ በጃባሊያ ከተማ ዙሪያ ያለውን ክፍት ቦታ እንደያዘ ተነግሯል።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከሦስት ወራት በላይ ቢሆነውም ትልቅ ወታደራዊ አቅም ያላት እስራኤል አሁንም በመላው ጋዛ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠማት ነው።

የአሜሪካ የስለላ ኤጀንሲዎች እንደገለጹት የእስራኤል ጦር ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑ የሐማስ ተዋጊዎችን እንደገደለ ይገምታሉ። ይህ ቁጥር ግን ኔታንያሁ ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከያዙት ዓላማ አንጻር እጅግ ያነሰ ነው።

ሐማስ አሁንም በእስራኤል ወታደሮች ላይ ለወራት ጥቃት ማድረስ የሚያስችለው በቂ መሣሪያ እንዳለው ተነግሯል። ይህም እስራኤል ሊገጥማት የሚችለውን የተራዘመ ጦርነት ያሳያል ተብሏል።

አዝጋሚው የጦሩ ግስጋሴ፤ የሐማስ ከፍተኛ አዛዥ እስካሁን አለመያዝም ወይም አለመገደል እና በ130 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት የእስራኤል ታጋቾች አለመለቀቅ በእስራኤል የፀረ-መንግሥት ቁጣን እያሳደገው ነው።

በሐማስ ቁጥጥር ስር ያሉ ታጋቾች ዘመዶች ተቃውሟቸውን በመቀጠል ኔታንያሁ ቡድኑን ለማጥፋት የያዙት ዓላማ በመተው ታጋቾች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የጸረ-ጦርነት ተቃዋሚዎችም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን ከሰንደቅ ዓላማቸው ዙሪያ እንጂ ከጠቅላይ ሚኒስትራቸው ዙሪያ አይደሉም ተብሏል። በቅርቡ በተደረገ የህዝብ አስተያየት መሰረት ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ኔታንያሁ በስልጣን ይቆዩ የሚሉት 15 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።

ጦርነቱ እንዴት ያበቃል የሚለው ጉዳይ በኔታንያሁ እና በእስራኤል ምዕራባውያን አጋሮች መካከል አለመግባባትን እየጨመረው ነው።