እስራኤል በቤይሩት ባደረሰችው ጥቃት 22 ሰዎች መሞታቸውን ሊባኖስ አስታወቀች

በቤሩት እስራኤል የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ጭስ ሲወጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል በማዕከላዊ ቤይሩት ሐሙስ አመሻሽ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 22 ሰዎች ሞተው 117 መቁሰላቸውን የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች ጥቃቱ በተፈጸመበት እና በመዲናይቱ የሺዓዎች መኖሪያ በሆነው ባቹራ አካባቢ ከፍተኛ ፍንዳታ መስማታቸውን ገልጸዋል። የነፍስ አድን ሠራተኞች በቦታው ፍርስራሾችን ለማንሳት ሲቆፍሩ ታይተዋል።

አምቡላንሶች ቁስለኞችን ወደ አሜሪካ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ወስደዋቸዋል።

ያልተረጋገጡ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንዳሉት ከሆነ ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው ዋፊቅ ሳፋን ነው። ግለሰቡ በቅርቡ የተገደሉት የሄዝቦላህ መሪ ሃሰን ናስራላህ አማች ሲሆኑ በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊም ጭምር ናቸው።

በጉዳዩ ዙሪያ የሄዝቦላህ የሚዲያ ቢሮ የሰጠው አስተያየት የለም።

የእስራኤሉ ጥቃት በባቹራ በርካታ ሰዎች የሚኖሩባቸው ንዌሪ እና ባስታ የተባሉ ሰፈሮች ውስጥ የሚገኙ የመኖሪያ ሕንፃዎችን ዒላማ ያደረገ ነው።

እስራኤል የሊባኖስ መዲና ቤይሩት ላይ ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰች ሲሆን ባለፉት ሁለት ቀናት አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ከቆየ በኋላ ነው የሐሙስ ምሽቱ ጥቃት የተሰማው።

ከጥቃቱ በፊት ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ ያልተሰጠ ሲሆን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (አይዲኤፍ) የሰጠው አስተያየትም የለም።

እስራኤል ከደቡባዊ የዳሂህ ዳርቻ ውጪ በከተማይቱ ላይ የአየር ጥቃት ስትፈጽም ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን ተደጋግሞ በደረሰው ጥቃት የሔዝቦላህ አዛዦችን ገድላ የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን አወድማለች።

ስሟ እንዳይገለፅ የፈለገች እና ከሆስፒታል ውጪ የነበረች ግለሰብ ፍንዳታዎቹ ከደረሱበት ህንጻ ጎን በሚገኝ ቤት እንደነበረች ትናግራለች።

የተጎዳው ህንጻ ሙሉ በሙሉ የመኖሪያ እንደነበር እና አራት ወይም አምስት ፎቆች እንደነበሩት ገልጻለች። ከዘመዶቿ መካከል አንዷ በጭንቅላቷ ላይ ጉዳት ደርሶባት ሕክምና እየተደረገላት እንደሆነም ተናግራለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቤይሩት ጥቃት የደረሰው በደቡባዊ ሊባኖስ ሁለት የኢንዶኔዥያ የሠላም አስከባሪ ኃይሎች ጉዳት ከደረሰባቸው ከሰዓታት በኋላ ነው። ጉዳቱን ያስተናገዱት የእስራኤል ታንክ በጥበቃ ማማ ላይ በመተኮሱ ነው ሲል የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል።

በናኩራ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጥበቃ ማማ በቀጥታ ተመትቶ ሰላም አስከባሪዎቹ እንዲወድቁ ምክንያት ሆኗል ሲል በሊባኖስ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ ሃይል (ዩኒፊል) በመግለጫው አስታውቋል።

ዩኒፊል በ1978 የተቋቋመ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ሲሆን ጦርነቶችን በመከታተል እና በደቡብ ሊባኖስ ውስጥ ለሚኖሩ ሲቪሎች ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ያገለግላል።

የእስራኤል ወታደሮች ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንብረቶችን “በተደጋጋሚ ደብድበዋል” ብሏል። የእስራኤል ወታደሮች በሌሎች ሁለት የዩኒፊል ካምፖች የሚገኙ ካሜራዎችን እና መብራቶችን ሆን ብለው ዒላማ አድርገዋል።

ሠራተኞቹ “በተከለሉ ቦታዎች” እንዲቆዩ ካዘዙ በኋላ ወታደሮቹ ከጣቢያው አካባቢ መተኮሳቸውን የእስራኤል ጦር ገልጿል።

ሁለቱም ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ላይ ከባድ ጉዳት ባይደርስባቸውም ሆስፒታል እንደሚገኙ የገለጸው የመንግስታቱ ድርጅት፤ በሠላም አስከባሪ ቡድኑ ላይ ሆን ተብሎ የሚሰነዘረው ጥቃት “የዓለም አቀፍ ህግን በእጅጉ መጣስ ነው” ብሏል።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ የእስራኤል ወታደሮች በናኩራ የሚገኘው የጦር ሰፈር ላይ በመተኮስ "የሠላም አስከባሪ ሃይሎች ተጠልለው የሚገኙበትን መግቢያ በር በመምታት ተሽከርካሪዎችን እና የግንኙነት ስርዓቱን ጎድተዋል" ሲል የተባበሩት መንግስታት አክሎ ገልጿል።

የእስራኤል ሰው አልባ አውሮፕላን ከሠላም አስከባሪው ሠፈር መግቢያ በላይ ሲበርም ታይቷል።

ሄዝቦላህ በበኩላ በናኩራ የምድር ዘመቻ ላይ ነበሩ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ሮኬቶችን በመተኮሱ ወደ አካባቢው የሚሄደውን ታንክ በማውደም ጉዳት ማድረሱን ተናግሯል።

ሄዝቦላህ ላይ መስከረም 11 የተከፈተው የምድር ዘመቻ እንደቀጠለ ሲሆን በሊባኖስ ውስጥ የሚዋጉ አራት የእስራኤል ክፍለ ጦሮች አሉ።

የዩኒፊል ቃል አቀባይ ሐሙስ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእስራኤል ጦር የሠላም አስከባሪ ወታደሮች ባሉበት አካባቢ የሚያደርገው እንቅስቃሴ “አስደንጋጭ” እና “በጣም አሳሳቢ” ነው።

በእስራኤል ኃይሎች የተመቱት ቦታዎች የተባበሩት መንግስታት ጣቢያ መሆናቸው ይታወቃሉ ያሉት አንድሪያ ቴኔንቲ “የተፈጠረውን ጉዳይ ለመረዳት ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር መወያየቱ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ዩኒፊል በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ "ብሉ ላይን (ሰማያዊ መስመር)" ተብሎ በሚጠራው አካበቢ ይንቀሳቀሳል። ቦታው ሊባኖስን ከእስራኤል እና በእስራኤል ቁጥጥር ስር የምትገኘውን ጎላን ሃይትስ የሚለይ ኦፊሴላዊ መስመር ነው።

ባለፈው ሳምንት ዩኒፊል ከሰማያዊ መስመር አካባቢው ለቅቆ እንዲወጣ በእስራኤል ጦር ትዕዛዝ ቢሰጠውም ፈቃደኛ አልሆነም።

ሊባኖስ ውስጥ ከ50 አገራት የተወጣጡ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ የዩኒፊል ሠላም አስከባሪ ወታደሮች ይገኛሉ። ወደ 800 የሚጠጉ ሲቪል ሰራተኞችም አሉ።

የተጎዱት የሠላም አስከባሪ ሃይሎች የመጡባት ኢንዶኔዢያ ከ1200 በላይ ወታደሮችን ለዩኒፊል በማዋጣት ቀዳሚ ናት።

ከአንድ ሺህ በላይ ወታደሮችን ለዩኒፊል ያዋጣው የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር ክስተቶቹን "የማይታለፉ" እና "በጥንቃቄ እና በቆራጥነት መወገድ አለባቸው" ብለዋል።

በሐሙስ ዕለት ብቻ ሄዝቦላህ 190 የሚጠጉ ሮኬቶችን ከሊባኖስ ወደ እስራኤል መተኮሱን አይዲኤፍ አስታውቋል።

የእስራኤል በምስራቃዊ ሊባኖስ የካራክ ግዛት በፈጸመችው የአየር ጥቃት አራት ሰዎችን ሲገደሉ 17 መቁሰላቸውን የሊባኖስ የህዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።

ባለፈው ዓመት እስከ 1.2 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው መሰደዳቸውን የሊባኖስ መንግስትገልጿል።