ሚሊዮን ዶላሮች ከሴቶች አጭበርብሯል የተባለው ግለሰብ ጆርጂያ ውስጥ ተያዘ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ኔትፍሊክስ በ2022 'ዘ ቲንደር ስዊንድለር' በሚል ርዕስ በለቀቀው ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንተሪ) አማካኝነት ታዋቂ የሆነው እና ከዚህ ቀደም በማጭበርበር ወንጀል ተፈርዶበት የነበረው ግለሰብ ጆርጂያ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ።

ሳይመን ሌቪቭ የተባለው እስራኤላዊ ግለሰብ፤ በሀገሪቱ ደቡብ ምዕራብ ክፍል በሚገኘው ማቱሚ አየር ማረፊያ ሲደርስ በቁጥጥር ስር እንዲውል የተደረገው በኢንተርፖል ጥያቄ መሰረት እንደሆነ የጆርጂያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሰኞ ዕለት አስታውቋል።

የ34 ዓመቱ ሌቪቭ የፈጸማቸውን በርካታ የፍቅር ግንኙነት ማጭበርበሮች እንዲሁም 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርሱ የተገመቱ የፋይናንስ ወንጀሎችን ያጋለጠው የምርመራ ዘጋቢ ፊልም ከተለቀቀ በኋላ ታዋቂነትን አትርፏል።

ግለሰቡ 'ቲንደር' በተባለው የፍቅር ግንኙነት ፈላጊዎች መገናኛ መተግበሪያ ላይ ራሱን እንደ ባለጸጋ የአልማዝ እንቁ ነጋዴ ልጅ አድርጎ ሲያቀርብ እንደነበር ተነግሯል። በዚህ መልኩ በማጭበርበር ሴቶችን ከቀረበ በኋላም ገንዘብ እንዲያበድሩት እንዳደረገ እና የተበደረውን ገንዘብ እንዳልመለሰ በፊልሙ ላይ ታይቷል።

ትክክለኛ ስሙ ሺሞን የሁዳ ሃዩት የሆነው ሌቪቭ ግን፤ የቀረቡበትን እነዚህን ውንጀላዎች ከዚህ ቀደም ውድቅ አድርጓል።

ባለስልጣናት ግለሰቡ በቁጥጥር ስር እንዲውል የተደረገበትን ዝርዝር ምክንያት እስካሁን ድረስ ይፋ አላደረጉም።

ሌቪቭ በ2019 ከዚህ ውጪ በሆኑ ሌሎች አራት የማጭበርበር መዝገቦች ተከስሶ 15 ዓመት ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም በእስር ቤት ውስጥ አምስት ወራትን ብቻ ካሳለፈ በኋላ ተለቅቋል።

'ይኔት' የተሰኘው የእስራኤል ድረ ገጽ እንዳስነበበው፤ የሌቪቭ ጠበቃ ደንበኛዬ "በዓለም ዙሪያ በነጻነት ሲጓዝ ነበር" በማለት ተናግረዋል።

ጠበቃው፤ "ከታሰረ በኋላ ዛሬ ጠዋት አናግሬዋለሁ፤ ነገር ግን እስካሁን [የተያዘበትን] ምክንያቱን አልተረዳንም" ብለዋል።

ሌቪቭ፤ ከ2017 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት የፈጠረውን ሀሰተኛ የኦንላይን ማንነት በመጠቀም እንዲሁም የግል ጄቶች እና ቅንጡ የበዓል አከባበሮችን ያካተተ የተቀናጣ የህይወት ዘይቤ እንዳለው በማሳየት ሴቶች ወደ ፍቅር ግንኙነት እንዲገቡ ሲያታልል ነበር።

በዶክመንተሪው ላይ ቀርበው ታሪካቸውን የተናገሩ ሴቶች፤ ሌቪቭ እምነታቸውን ለማግኘት ሲል በውድ ስጦታዎች እና በቅንጦት ጉዞዎች ያንበሸብሻቸው እንደነበር ገልጸዋል።

በመጨረሻም ግለሰቡ "ጠላቶች" እያሳደዱት እንደሆነ በመግለጽ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲልኩለት ካደረገ በኋላ ግንኙነቱን እንደሚያቋርጥ ተናግረዋል።

በኔትፍሊክት ዘጋቢ ፊልም ላይ ከቀረቡት ሴቶች አንዷ ከሌሊቭ ጋር በነበራት ግንኙነት ወቅት ከ270 ሺህ ዶላር በላይ እንደሰጠችው ጠቅሳለች።

ባለፈው ዓመት ደግሞ አይሬን ትራኖቭ የተባለች ሌላ ሴት ያበደረችውን 31 ሺህ ፓውንድ እንዳልመለሰ በመግለጽ እስራኤል ውስጥ የ91 ሺህ ፓውንድ ክስ መስርታለች።

ሌሊቭ በበኩሉ በዶክመንታሪው ላይ የቀረበበትን ውንጀል አጥብቆ ውድቅ እንደሚያደርግ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግሯል።

'ዘ ቲንደር ስዊንድለር' የተባለው ዘጋቢ ፊልም በየካቲት 2022 በተለቀቀበት ወቅት በ90 ሀገራት ውስጥ ብዙ ሰዎች የተመለከቱት የኔትፍሊክስ ዶክመንታሪ ሆኖ ነበር።