ትራምፕ ‘አሜሪካ ዩክሬንን ከመደገፏ በፊት የትምህርት ቤቶቿ ደኅንነት ላይ ታተኩር’ አሉ

ታትሟል

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የትምህርት ቤቶችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የምታወጣው የገንዘብ ድጋፍ ለዩክሬን ከሚቀርበው እርዳታ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ይህ የትራምፕ ንግግር የተሰማው በቴክሳስ ግዛት በትምህርት ቤት ውስጥ 19 ህጻናት ሁለት መምህራኖቻቸው በአንድ በታጠቀ ወጣት ከተገደሉ በኋላ ነው።

የጦር መሣሪያን በተመለከተ እየተካሄደ በሚገኝ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ፣ አሜሪካ ወደ ዩክሬን ቢሊዮን ዶላሮችን መላክ ከቻለች “በአገራችን ውስጥ ያሉ ልጆቻችንን ደኅንነት ለመጠበቅ እንዲውል የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን” ብለዋል።

“በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ትሪሊዮን ዶላሮችን ብናፈስም ጠብ ያለ ነገር ግን ያለም” ያሉት የቀድሞ ፕሬዝዳንት፣ በከፍተኛ ጭብጨባ የታጀቡ ሲሆን “የተቀረውን ዓለም ከመገንባታችን በፊት በአገራችን ለልጆቻችን ደኅንነቱ የተጠበቀ ትምህርት ቤት ልንገነባ ይገባል” ሲሉም አክለዋል።

በዚህ ወር መግቢያ ላይ የአሜሪካ ምክር ቤት ለዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ የሚውል 40 ቢሊዮን ዶላር እንዲላክ ወሰኗል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ ጀምሮ ምክር ቤቱ በድምሩ 54 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን አጽድቋል።

ትራምፕ የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን የተቃወሙ ሲሆን ሰላማዊ አሜሪካውያን ራሳቸውን “ከመጥፎ” ሰዎች እንዲከላከሉ ሊፈቀድላቸው ይገባል ብለዋል።

በጦር መሳሪያ ላይ ቁጥጥር ከማድረግ ይልቅ በትምህርት ቤትች ከላይ እስከ ታች የሚዘረጋ የደኅንነት ሥርዓት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

እንደሳቸው ገለጻ፣ በትምህርት ቤቶች መግቢያ ላይ ብረት ነክ ነገሮችን የሚለዩ መሣሪያዎችን ማስቀመጥ እና ቢያንስ አንድ የታጠቀ ፖሊስ እንዲኖር ማድረግን ጨምሮ የተጠናከረ ጥበቃ ሊኖር ይገባል።

ይህ እንዳይሆን እንቅፋት የሆኑት ዲሞክራቶች ናቸው ሲሉም ከሰዋል።

ትራምፕ ንግግራቸውን ከመጀመራቸው በፊት በቅርቡ በአሜሪካ ትምህርት ቤት በተፈጸመ ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ስም ዘርዝረዋል።