ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ተኩስ የከፈተን ግለሰብ ተኩሳ የመታች ሴት የብዙዎችን ሕይወት አዳነች
አሜሪካ ውስጥ በድግስ ታዳሚዎች ላይ ተኩስ የከፈተን ግለሰብ ተኩሳ የመታች አንዲት ሴት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እንዳዳነች ፖሊስ ተናገረ።
ግለሰቡ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ሰዎች ያሉበት ድግስ ላይ ጥቃት ለማድረስ መተኮስ ሲጀምር፣ በአካባቢው የነበረችው ሴት ከቦርሳዋ መሣሪያ አውጥታ ተኩሳበታለች።
ግለሰቡ በዌስት ቨርጂኒያ፣ ቻርልስተን በፍጥነት እያሽከረከረ ሲጓዝ በአካባቢው ልጆች ስላሉ ዝግ እንዲል ቢጠየቅም፣ ኋላ ላይ ተመልሶ ድንገት ድግሱ በነበረበት አካባቢ አውቶማቲክ መሳሪያ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሮ ነበር።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ቶኒ ሀዝሌት እንዳሉት፣ ሴቲቷ በፍጥነት መሣሪያ አውጥታ ግለሰቡ ላይ በመተኮሷ የብዙዎችን ሕይወት አድናለች።
ግለሰቡ ኤአር-15 የሚመስል መሣሪያ ይዞ፣ ከመኪና ውስጥ ሆኖ መተኮስ ሲጀምር፣ የልደት እና የምርቃት ሥነ ሥርዓት በአካባቢው እየተካሄደ ነበር።
ግለሰቡን የተኮሰችበት ሴት ማን እንደሆነች ይፋ ባይደረግም፣ ፖሊስ እንዳልሆነች ግን ተገልጿል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ “መሣሪያ በሕግ አግባብ ይዛ የተገኘች የማኅበረሰቡ አካል ናት። ከአካባቢው ከመሸሽ ይልቅ አጥቂውን ተጋፍጣ የብዙዎችን ሕይወት ታድጋለች” ብለዋል።
ግለሰቧ በአካባቢው ቆይታ ለፖሊስ ምርመራ እንደተባበረችና ክስ እንደማይመሠረትባትም ተገልጿል።
ሊፈጽም የነበረው ዴኒስ በትለር የተባለው የ37 ዓመቱ ግለሰብም በተኩሱ እዚያው ሕይወቱ አልፏል።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በወንጀል ተጠርጥሮ ታስሮ እንደነበርም ፖሊስ አስታውቋል።
ዴኒስ በምን መንገድ መሣሪያውን እንዳገኘ እስካሁን አልታወቀም። ከዚህ ቀደም የወንጀል ፍርደኛ እንደመሆኑ መሣሪያ እንዲታጠቅ ሕጉ አይፈቅድለትም።
ባለፈው ሳምንት በቴክሳስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተኩስ ተከፍቶ ከ20 በላይ ሕጻናትና አዋቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ አሜሪካ ውስጥ ስለ መሣሪያ ቁጥጥር ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቷል።
21 ሰዎች ከሞቱበት የቴክሳሱ ጥቃት ጀርባ ያለው ታዳጊ፣ ተኩስ የከፈተው ኤአር-15 የተባለ መሳሪያን በሕገ ወጥ መንገድ ገዝቶ እንደሆነ መገለጹ አይዘነጋም።