ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሦስት እስራኤላውያን በስለት እና በመኪና ጥቃት በፍልስጤማዊ ተገደሉ
በዌስት ባንክ የአይሁዶች ሰፈር አቅራቢያ በፍልስጤማዊ በደረሰ በስለት መወጋት እና በመኪና የመግጨት ጥቃት ሦስት እስራኤላውያን ተገድለዋል ሲል የእስራኤል ጦር አስታወቀ።
ጥቃት አድራሹ ሰላማዊ ሰዎችን በመኪና ከመግጨቱ በፊት በኢንዱስትሪ ዞን እና በነዳጅ ማደያ አካባቢ በስለት ሁለቱን ሰዎች እንደወጋ ተዘግቧል።
የ18 ዓመቱ ጥቃት አድራሽ በእግሩ ለመሸሽ ሲሞክር በጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።
ጥቃቱ የደረሰው አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥት ለመመስረት በሂደት ላይ ባሉበት ወቅት ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደው ምርጫ በቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመራው ቡድን ስልጣኑን ለመረከብ የሚያስችለውን በቂ መቀመጫዎችን አግኝቷል። ቡድኑ የቀኝ አክራሪ ፓርቲ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን አንዱ መሪ 'አሸባሪዎችን ከሃገር ለማባረር' ቃል ገብተዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (አይዲኤፍ) እና የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ጥቃት አድራሹ በማዕከላዊ ዌስት ባንክ በሚገኘው አሪየል ኢንዱስትሪያል ዞን ደጃፍ የነበረን የጥበቃ ሠራተኛ በስለት ከወጋ በኋላ በአቅራቢያው በሚገኝ የነዳጅ ማደያ ተጨማሪ ሰው አጥቅቷል።
በኋላም መኪና ሰርቆ ሌሎችን ገጭቶ በስፍራው ያሉትንም መውጋቱን እንደቀጠለ ተነግሯል። ጥቃት አድራሹ ለማምለጥ ሲሞክር በጥይት ተመትቶ ከመሞቱ በፊት ሁለተኛ መኪና ሰርቆ ሌላ አደጋ ማድረሱ ተነግሯል።
በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁለት ሰዎች በስለት ተወግተው ሲሞቱ ሦስተኛው እና በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኘው ግለሰብ በመኪና ግጭቱ ህይወቱ ማለፉን የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንዳሉት ጥቃት አድራሹ በኢንዱስትሪ ዞኑ በፅዳት ሠራተኛነት የሚሠራና በአቅራቢያው ከምትገኘው ሃሪስ መንደር የመጣ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመረጡት ኔታንያሁ በትዊተር ገፃቸው “ለተጎዱት ሰዎች ጸሎቴ ይድረስ… በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን የጸጥታ ኃይሎችን እናጠናክራለን” ሲሉ አስፍረዋል።
ኔታንያሁ በሚያቋቁሙት መንግሥት የህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ለመሆን የሚፈልጉት ቀኝ አክራሪው የኦትዝማ ይሁዲት (የአይሁድ ኃይል) ፓርቲ መሪ ኢታማር ቤን-ጊቪር ጥቃቱ ለአዲሱ መንግሥት የማንቂያ ደወል ነው ብለዋል።
"ሽብርተኝነትን ለማጥፋት የሞት ቅጣት ሕግ መፅደቅ አለበት። ሽብርተኝነትን የሚያጠፋው ጠንካራ ውሳኔ ብቻ ነው" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።