የኬንያዋ ሴናተር ‘ልብሳቸው የወር አበባ በመንካቱ’ ከፓርላማ እንዲወጡ ተደረጉ

የኬንያዋ ሴናተር

የፎቶው ባለመብት, Twitter

ታትሟል

የኬንያዋ ሴናተር የወር አበባን አስመልክቶ በሚያደርጉት ዘመቻ ደም የነካው ነጭ ልብስ በመልበሳቸው ከፓርላማ እንዲወጡ ተደረጉ።

ሴናተሯ ግሎሪያ ኦርዎባ ማክሰኞ የካቲት 7፣ 2015 ዓ.ም ደም የነካው ነጭ ልብስ ለብሰው ፓርላማ የተገኙት የንጽህና መጠበቂያን በተመለከተ ለምክር ቤቱ የሚያቀርቡት ረቂቅ ህግ ስለነበር ነው።

የገዥው ጥርም ፓርቲ አባል የሆኑት ግሎሪያ የንጽህና መጠበቂያን ማግኘት የሁሉም ሴቶች መብት እንደሆነና ነጻ ፓድም ለተማሪዎች መንግሥት ሊያቀርብ እንደሚገባም የያዘ ረቂቅ ህግም ይዘው ነበር የተገኙት።

የምክር ቤቱ አባላት ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የነበረውን ስብሰባም በማቋረጥ ለአፈ ጉባኤው ሴናተሯ ‘ተገቢ ያልሆነ አለባበስ’ እንደለበሱ መናገራቸው ተዘግቧል።

ሴናተሯ በበኩላቸው “አንድ ሰው እዚህ ቆሞ አንዲት ሴት ልብሷ የወር አበባ በመንካቱ ምክር ቤቱ ተዋርዷል ብሎ መናገራቸው ያስገርመኛል” ሲሉም ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

የፓርላማው አፈ ጉባኤ አማሶን ኪንግ ሴናተሯ ረቂቅ ህጉን ለማቅረብ ወደ መድረኩ ከመጠጋታቸው በፊት ልብሳቸውን እንዲቀይሩ አዘዋቸዋል።

“የወር አበባ ፈጽሞ ወንጀል አይደለም። ሴናተር ግሎሪያ ተፈጥሯዊው የወር አበባ ወቅት ላይ በመሆንሽና ልብስሽ በመበላሸቱ አዝናለሁ።እናም ወጥተሽ ልብስሽን ቀይረሽ እንድትመጪ እጠይቃለሁ” ሲሉም አፈ ጉባኤው ተናግረው ነበር

ሴናተሯ እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ ለጋዜጠኞች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“በወር አበባ ምክንያት ለዘመናት እያጋጠመ ያለው መገለል እንዲቆም እንጠይቃለን። በድህነታቸው ምክንያት የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ የማያገኙ ተማሪዎች ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ እየጠየቅን ነው። እኔ እየተሟገትኩ ያለሁት ተማሪዎች በሙሉ የንጽህና መጠበቂያ በነጻ እንዲያገኙ ነው” ብለዋል።