አይኤስ መሪው መሞቱንና ተተኪውንም አስታወቀ

ታትሟል

የእስላማዊ መንግሥት ቡድን (አይኤስ) መሪው አቡ አል ሐሰን አል ሃሽሚ አል ቁራይሺን መሞቱን አስታወቀ።

ከቡድኑ ቃለ አቀባይ በወጣ የድምፅ መልዕክት መሪው የተገደለው “የአምላክ ጠላቶች” በሚል የጠራቸውን ሲዋጋ ነው ቢልም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

አሜሪካ በበኩሏ መሪው የተገደለው አማጺው የፍሪ ሶሪያ ጦር ጥቅምት አጋማሽ ላይ በደቡብ ምዕራብ ሶሪያ ባካሄደው ዘመቻ መሆኑን አስታውቃለች ።

ግለሰቡ የቡድኑ መሪነት ስልጣን የተቆጣጠረው በባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር።

 ከሱ በፊት የነበረው መሪ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ አሜሪካ ባደረገችው ከበባ ራሱን ካጠፋ በኋላ መሆኑም ተገልጿል ።

ተተኪው መሪ ቃለ አቀባዩ አል- ሁሴን አል ሁሴይኒ አል ቁራይሺ የሚባል እንደሆነ ገልጿል።

እንደ ከዚህ ቀደሙም ቃለ አቀባዩ የአዲሱን መሪ ትክክለኛ ስሙን፣ ዜግነቱን እንዲሁም ታሪኩን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

አቡ አል ሑሴይንን “ከአንጋፋዎቹ ጂሃዲስቶች አንዱ”በማለት ያሞካሸው ቃለ አቀባዩ የቡድኑ ደጋፊዎች ታማኝነታቸውን እንዲያሳዩም ጠይቋል።

ስለ ቀድሞው መሪ አቡ አልሐሰን ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም፤ መሪም ከሆነ በኋላም በስሙ መግለጫ አውጥቶ አያውቅም።

ነገር ግን ሰኞ እለት የጂሃዲስት ቡድን አልቃይዳን የሚደግፍና ጸረ አይኤስ ቴሌግራም ቻናል “ከተወሰነ ጊዜ በፊት” መገደሉን አሳውቋል። 

የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላዊ ዕዝ በሰጠው መግለጫ አቡ አል ሐሰን በደቡብ ምዕራብ ሶሪያ ግዛት ዴራ በተባለው ስፍራ በፍሪ ሶሪያ ጦር መገደሉን ነው።

 ይህ ጦር  በሃገሪቱ የርስ በርስ ጦርነት ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድን ከስልጣን ለመገልበጥ የሚዋጉ ኃይሎች ናቸው።

በዚህ ወታደራዊ ዘመቻ ምንም አይነት የአሜሪካ ጦር አልተሳተፈም ሲሉ የወታደራዊ ቃል አቀባይ አክለው ገልጸዋል።