ዩናይትድ የጀርመኑን ኃያል ቡድን አሸንፎ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ይቻለዋል?

ten hag

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ማንቸስተር ዩናይትድ ወሳኝ የሆነ ፍልሚያ የሚያደርግበት ጠንካራ ግጥሚያ ዛሬ ማክሰኞ ታኅሣሥ 2/2016 ዓ.ም. ምሽት ይጠብቀዋል።

ቡድኑ ወደ ቀጣዩ የቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ዙር ለመግባት ኃያሉን የጀርመኑን ክለብ ባየር ሙኒክን ማሸነፍም ብቻ ሳይሆን፤ የኮፐንሃገን እና ጋላታሳራይ አቻ መለያየትን ይጠብቃል።

በዚህ ምድብ ሙኒክ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ኮፐንሃገን እና ጋላታሳራይ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በአምስት ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ዩናይትድ ደግሞ በአራት ነጥብ መጨረሻው ደረጃ ላይ ይገኛል።

ዩናይትድ የቀጣይ ዙር የቻምፒየንስ ሊግ ተስፋው እጅጉን የጠበበ ቢሆንም የክለቡ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ግን “የትኛውንም ተጋጣሚ ማሸነፍ እንችላለን” ብለዋል።

በምድቡ ከአምስት ጨዋታዎችን አንዱን ብቻ ማሸነፍ የቻለው ቡድን አሠልጣኝ፤ “በትክክለኛው መነሳሳት ላይ ካለን የትኛውንም ተጋጣሚ ማሸነፍ እንችላለን” ሲሉ የቡድናቸውን ዝግጁነት ለማጠናከር ሞክረዋል።

ዩናትድ

ማንችስተር ዩናይትድ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉ ቀርቶ የዩሮፓ ሊግ ተሳታፊነቱን ሊያጣ የሚችልበት አጋጣሚም ሰፊ ነው።

አራት ክለቦችን ከሚይዘው ምድብ ቀዳሚ ሁለት ቡድኖች ወደ ቀጣይ የጥሎ ማለፍ ዙር ሲያልፉ፤ ሦስተኛ ደረጃን የሚይዘው ደግሞ በአውሮፓ ሊግ የመጫወት ዕድል እንዳለው ይታወቃል።

ዩናይትድ በሙኒክ ከተሸነፈ ከአውሮፓ መድረክ ሙሉ በሙሉ ተሰናባች ይሆናል። ይሁን እንጂ ዩናይትድ ከሙኒክ አቻ ተለያይቶ ጋላታሳራይ ኮፐንሃገንን ካሸነፈ፤ ዩናይትድ በኦልትራፈርድ ኮፐንሃገንን በማሸነፉ በአውሮፓ ሊግ ተሳታፊ የሚሆንበት ዕድል አለው።

በሌሎች ጨዋታዎች ከምድብ 1 እስከ 4 ያሉት የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ይካሄደሉ።

በምድብ 2 ቀድሞ በአንደኛነት ማለፉን ያረጋገጠው አርሰናል ፒኤስቪን ይገጥማል። ፒኤስቪ አይንድሆቨን ከአርሰናል አቻ መለያይት ወይም በጠባብ ውጤት መሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉን ያረጋግጥለታል።

ቀጣይ ተጠባቂው ጨዋታ በምድብ 3 የሚገኙት ናፖሊ እና ብራጋ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው። ብራጋ ከሜዳው ውጪ ናፖሊን ገጥሞ በሰፊ የግብ ልዩነት የሚያሸንፍ ከሆነ ወደ ቀጣይ ዙር ያልፋል።

ዩኒየን በርሊን ደግሞ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፈ ዕድሉ እጅግ ጠባብ ሲሆን፤ ይህም በብራጋ እና በናፖሊ ጨዋታ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ማድሪድን ማሸነፍ የሚችል ከሆነ የአውሮፓ ሊግ ተሳታፊነቱን ሊያረጋግጥ ይችላል።

በ11 ነጥብ የምድብ አራት መሪዎች የሆኑት ሪያል ሶሲዳድ እና ኢንተር የሚያደርጉት ፉክክርም በጉጉት ይጠበቃል።

በግብ ክፍያ ሪያል ሶሲዳድ የምድቡ መሪ ሲሆን፣ የምድቡ መሪ ሆኖ ለመጨረሰ በሚደረገው ትግል ከኢንተር ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀዋል።