አስደናቂው የ100 ሜትር ፉክክር እንዲሁም ተጠባቂው የ5 ሺህ እና 800 ሜትር ፍፃሜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/World Athletics
አሜሪካዊው የአጭር ርቀት ኮከብ ኖዋህ ላይልስ በሽርፍራፊ ስከንዶች ልዩነት የ100 ሜትር ኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነ።
ላይልስ በአስደናቂ ሁኔታ አሸናፊው በፎቶ በተለየበት ውድድር ጃማይካዊውን ኪሻኔ ቶምፕሰን በመርታት ነው የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው።
ሁለቱም አትሌቶች የ100 ሜትሩን ውድድር በ9.79 ሰከንድ ቢያጠናቅቁም ላይልስ በአምስት አንድ ሺህኛ ሰከንድ ቀድሞ በመግባት ድል ተቀዳጅቷል።
በኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው ቶምፕሰን ውድድሩን እየመራ ቢዘልቅም በመጨረሻዎቹ ሰከንዶች በላይልስ ተበልጧል።
በፓሪስ ኦሊምፒክ በአራት የተለያዩ ውድድሮች አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ለማምጣት እየተፎካከረ ያለው ላይልስ የመጀመሪያውን በድል ተወጥቷል።
አሜሪካዊው የቀድሞው የዓለም ሻምፒዮና ፍሬድ ከርሊ በ9.81 ሰከንድ ሶስተኛ ሲወጣ ደቡብ አፍሪካዊው አካኒ ሲምቢኔ አራተኛ ሆኖ አጠናቋል።
ስታድ ደ ፍራንስ የነበረው ጢም ያለው ተመልካች በጉጉት ሲጠባበቀው የነበረው የ100 ሜትር ፍፃሜ ለደቂቃዎች አርፍዶ ቢጀምርም አስደናቂ ውድድር አሳይቷል።
በጣም ፉክክር በተስተዋለበት ፍልሚያ ስምንቱም ተፋላሚዎች ከላይልስ በ0.12 ሰከንድ ልዩነት ነው የገቡት።
የብሪታኒያዎቹ ዣርኔል ሂዩስ እና ሉዊ ሂንችክሊፍ ወደ ፍፃሜው ማለፍ ሲሳናቸው ያለፈው ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ማርሴል ጄኮብስ እና ጃማይካዊው ኮከብ ኦብሊክ ሴቪል ከሜዳሊያ ፉክክሩ ውጭ ሆነዋል።
ባለፈው ዓመት የዓለም ሻምፒዮን በግሉ እና በቡድን በጠቅላላው ሶስት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት የቻለው ላይልስ ውድድሩን ካጠናቀቀ በኋላ በግዙፉ የስታድየሙ የቴሌቪዥን መስኮት ውጤት እስኪታይ ድረስ በጉጉት ሲጠባበቅ ታይቷል።
የ27 ዓመቱ አሜሪካዊ ከድሉ በኋላ አሸናፊዎች የሚያጩሁትን ደወል በተደጋጋሚ በመምታት ደስታውን ከገለጠ በኋላ ባንዲራውን እያውለበለበ ስታዲየሙ ውስጥ ሲዞር ነበር።
ላይልስ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በ100 ሜትር እና በ200 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ ከዩዜይን ቦልት በኋላ የመጀመሪያው ሯጭ ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሰኞ ምሽት ውድድሮች
የፓሪስ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድሮች ሰኞ ሐምሌ 29/2016 ቀጥለው ሲካሄዱ ኢትዮጵያዊያን ሯጮች በማጣሪያ እና በፍፃሜ ይሳተፋሉ።
ምሽት ከ2 ሰዓት ጀምሮ በ3000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያ የርቁተ ክብረ-ወሰን ባለቤት ለሜቻ ግርማ እና የሀገሩ ልጅ ሳሙዔል ፍሬው ይሮጣሉ።
የርቀቱ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት የሆነው ለሜቻ፤ በፍፃሜው እንደሚያልፍ የሚጠበቅ ሲሆን ድል የሚቀናው ከሆነ በኦሊምፒክ መድረክ በ3 ሺህ ሜትር ወርቅ ያመጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, World Athletics
ሌላኛው ተጠባቂ ውድድር ምሽት 4 ሰዓት ከሩብ አካባቢ የሚካሄደው የሴቶች የ5000 ሜትር ፍፃሜ ነው። የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ጉዳፍ ፀጋይ፣ መዲና ኢሳ፣ እና እጅጋየሁ ታዬ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።
ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፐየጎን እንዲሁም የሀገሯ ልጆች ቼቤት ቢያትሪስ እና ማርጋሬት ቼሊሞ ለሜዳሊያ የሚፎካከሩ ሯጮች ናቸው።
ከ5000 ሜትር ፍፃሜ በኋላ ተከትሎ የሚመጣው የ800 ሜትር የሴቶች ፍፃሜ ሲሆን ኢትዮጵያዊያኑ ፅጌ ዱጉማ እና ወርቅነሽ መሰለ ይሳተፋሉ። ኬንያዊቷ ሞራ ሜሪ ጠንካራ ተፎካካሪ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።
በሌሎች የመም [ትራክ] ውድድሮች በ200 ሜትር የሴቶች እና የወንዶች ማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
በኦሊምፒክ የእግር ኳስ ውድድር ደግሞ በግማሽ ፍፃሜው ሞሮኮ ከስፔን ምሽት 1፡00፤ ፈረንሳይ ከግብፅ ደግሞ ምሽት 4፡00 ይጫወታሉ።












