በመተከል ዞን ታጣቂዎች በተፈፀሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

የመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ

የፎቶው ባለመብት, Gilgel Beles Town Administration

የምስሉ መግለጫ, የመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጥቃቱ የተፈፀመው ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 6/ 2018 ዓ. ም. ጠዋት 12 ሰዓት ላይ በዞኑ ዋና ከተማ ግልገል በለስ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት እና መናኸሪያ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ "ሕይወቱ ያለፈም፣ ከባድም ቀላልም ጉዳት የደረሰበትም ሰው አለ" ያሉ አንድ ነዋሪ "11 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን" እንደሰሙ ጠቅሰዋል።

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር "በትክክል አለመታወቁንም" ተናግረዋል።

"በገብርኤል እና በማሪያም እበያተ ክርስቲያን፣ በመስቀል አደባባይ ላይም ሞርታር መሣሪያ ተጥሎ" በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪው ተናግረዋል።

ወደ ከተማው በእግር የገቡ "አሸባሪዎች" ያሏቸው ታጣቂዎች በአድማ በታኝ እና በመከላከያ ኃይል "መመለስ መቻሉን" ተናግረዋል።

የመተከል ዞን አስተዳደር በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ አጥቂዎቹ "የጉሙዝ ታጣቂዎች እና የፋኖ ኃይሎች" መሆናቸውን ጠቁሞ ጥቃቱ ግን "መክሸፉን" ገልጿል።

ዞኑ፤ ታጣቂዎቹ ወደ ግልገል በለስ ከተማ ለመግባት እና በንጹኃን ዜጎች ላይ ጉዳት ለማድረስ "ሙከራ" ማድጋቸውን ባወጣው አጭር መግለጫ ጠቅሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዞኑ ይህን ቢልም እንኳን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በከባድ መሣሪያ በታገዘው ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

ጥቃቱን ከፈጸሙት ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የገለጹት ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ የአካባቢው ነዋሪ "ቀይ ሰው ከዚህ አካባቢ ይውጣልን ነው የሚሉት" በማለት የጥቃቱ ዓላማ "ብሔር ተኮር" እንደሆነ ተናግረዋል።

በመናኸሪያ እና በእብያተ ክርስቲያናት ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው "ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች" ስለሆኑ ነው ብለውም ያምናሉ።

በታጣቂዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል "ሰዓታት የወሰደ" የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገም ነዋሪው ተናግረዋል።

መናኸሪያ አካባቢ የተጎዱት ሰዎች ወደተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎች መሆናቸውን አክለዋል።

በቤተ ክርስቲያን የተጎዱት "የሃይማኖት አባቶች" መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስከ ንጋት አንድ ሰዓት ድረስ የተኩስ ልውውጥ እንደቀጠለ እና ከዚያ በኋላ "አካባቢው ሰላም እንደሆነ" ገልጸዋል።

ሆኖም ግን "ነገ ለሚያጋጥመው ምንም ዋስትና የለንም" ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ ነዋሪ ደግሞ መናኸሪያ ሄደው አስከሬን ማንሳታቸውን ተናግረው፤ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ፓዊ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪው የተኩስ ልውውጡ እስከ "ሦስት ሰዓት ድረስ" እንደቀጠለ እና መናኸሪያ አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት "ከስምንት በላይ ሰዎች እንደሞቱ" ተናግረዋል።

"ከባድ ጉዳት ነው የደረሰው። እኔም መናኸሪያ የነበረውን በዐይኔ አይቻለሁ። ከስምንት በላይ ሰዎች እዚያው ሞተው ወድቀዋል። ቁስለኞቹ በሀይሩፍም፤ በአባዱላም እየተጫኑ ወደ ፓዊ ሆስፒታል ተወስደዋል። ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እኛም ሁለት ቁስለኞችን ወደ ሐኪም ቤት አስገብተናል" ብለዋል።

ወደ ማንኩሽ እና አሶሳ የሚጓዙ ሰዎች በመናኸሪያው ውስጥ እንደነበሩ እና "ሁለት ሞርተር ተተኩሶ አንደኛው እንደፈነዳ" ተናግረዋል።

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ንጹኃን ሰዎች እንደሆኑ የተናገሩት ነዋሪው "ቀድሞ እርምጃ መወሰድ" እንደነበረበት ሳይጠቅሱ አላለፉም።

አብዛኞቹ ሟቾች ወጣቶች እና መንገደኞች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ነዋሪዎች አካባቢው አሁን መረጋጋቱን የተናገሩ ሲሆን፤ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከተማውን መቆጣጠራቸውንም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ነዋሪዎቹ አሁንም ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

"እንዲህ ዓይነት ነገር ግልገል በለስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተለመደ ነው። እንደዚህ ተኩሶች ይደረጋሉ። የሆነ ያህል ሕዝብ ይሞታል። ከዚያ በኋላ በነጋታው ሕዝቡ እንደ አዲስ ሥራውን ይጀምራል።

"የፀጥታ አካላት አሁን ላይ ምንም የሉም ማለት ይቻላል። ሰው የለመደው ነገር ስለሆነ ወጥቶ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው" ሲሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ከዞኑ አስተዳዳር እና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሥልጣናት ስለጥቃቱ እና ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ምላሽ አላገኘም።

በመተከል ዞን እንዲህ ዓይነት ተደጋጋሚ ጥቃቶች የሚፈጸሙ ሲሆን፤ ባለፈው ግንቦት እና ሚያዚያ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ እና በማረሚያ ቤት ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የምትዋሰንበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚገኝበት ሲሆን፣ ድንበር ተሻግረው የሚመጡ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጽማሉ።