እስራኤል አርብ ንጋት ላይ በቤይሩት በፈጸመችው ከባድ ጥቃት ማንን ዒላማ አደረገች?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሐሙስ ሌሊት ለአርብ አጥቀቢያ እስራኤል ቤይሩት ውስጥ በፈጸመችው ከባድ የአየር ጥቃት የሔዝቦላ የግንኙነት አዛዥ የሆነው ሙሐመድ ራሺድ ስካፊ መገደሉን የእስራኤል መከላከያ ኃይል ተናግሯል።
የእስራኤል መከላከያ ስካፊ ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ በሄዝቦላህ ውስጥ እንደነበር እና ከቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ነበር ብሏል።
ሄዝቦላህ በግድያው ላይ እስካሁን ድረስ አስተያየት አልሰጠም።
እስራኤል ከፍተኛ መጠን ያላቸው 11 ቦምቦችን በመጠቀም ነበር ቤይሩትን የደበደበችው።
ይህ ጥቃት የተሰነዘረው ዐርብ ሊነጋጋ ሲል ሲሆን፣ ፍንዳታውም ከፍተኛ ነበር ተብሏል።
ፍንዳታው የተከሰተው ከቤይሩት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ብዙም ሳይርቅ ነው።
በተያያዘ መረጃ በእስራኤል የአየር ጥቃት ባለፈው ሳምንት የተገደሉትን የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህን ይተካል ተብሎ የሚጠበቀውን ሐሸም ሳፌይዲን ዒላማ ያደረገ እንደነበር ተገለጿል።
ሐሸም ሳፌይዲን የሐሳን ናስራላህ የቅርብ ዘመድ ናቸው።
የእስራኤል ባለሥልጣናት ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደገለጹት ሳፌይዲን ከከፍተኛ የሄዝቦላህ መሪዎች ጋር በዳሄይህ በሚገኝ አንድ ምሽግ ውስጥ ስብሰባ ላይ ነበሩ።
ይህ ስፍራ ባለፈው ሳምንት ሐሳን ናስራላህ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉበት ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/SHUTTERSTOCK
በሊባኖስ የክራይሰስ ግሩፕ ተንታኝ ዴቪድ ዉድ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራሮች እስራኤል ተደጋጋሚ ጥቃት በምታደርስበት አካባቢ ስብሰባ ማድረጋቸው “ከፍተኛ አደጋ” እንዳለው ይገልጻሉ።
ነገር ግን “ታጣቂ ቡድኑ የተሻለ አማራጭ የለውም” ሲሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ይገልጻሉ።
“ይህንን ለመረዳት የሄዝቦላህ ፔጀሮች ላይ የደረሰውን ፍንዳታ መለስ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል።የእስራኤል ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቡድኑ ውስጥ ሰርገው መግባታቸውን እና የሄዝቦላህ አመራሮች ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመነጋገር መገደዳቸውን መረዳት ይቻላል። ከዳሄህ ውጭ የት ሊሄዱስ ይችላል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
አካባቢው በጥልቀት የተቆፈሩ የሄዝቦላህ ምሽጎች የሚገኙበት ነው።
ነገር ግን እነዚህ ምሽጎች የተሠሩት የሄዝቦላ ከፍተኛ አመራሮችን ከእስራኤል የአየር ጥቃት መሸሸግ ይችላሉ ተብሎ በታመነበት ጊዜ ነው።
“መሸሸጊያዎቹ ግን አሁን ብናኝ ሆነዋል” ይላሉ ዉድስ።
እስካሁን ድረስ ሳፌይዲን ዒላማ ስለመሆናቸው የተሰጠ ይፋዊ ማረጋገጫ የለም።
ዉድ ግን “አንዱን የሄዝቦላህ መሪ ወይንም ሌላውን ዒላማ ማድረግ ብቻ አይደለም፤ በርካታ መሪዎችን በአንድ ጊዜ ማጥቃት ነው ዕቅዱ። ይህ ነው ለሔዝቦላ እንደ ድርጅት ዋነኛ የታሪክ እጥፋት የሆነው።”
ሐሻም ሳፌይዲን ማን ነው?
ሐሻም ሳፌይዲን የሄዝቦላህ መሪ የነበሩት ሐሳን ናስራላህን ይተካል ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ የጂሃድ ምክር ቤቱ እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚው ምክር ቤት ኃላፊ በመሆን የወታደራዊ እና ደኅንነት ተግባራትን በመምራት እና በማደራጀት ኃላፊነት ተጥሎበታል።
ሳፌይዲን የሄዝቦላህ መሪ የነበሩት ሐሳን ናስረላህ የቅርብ ዘመድ ሲሆን፣ በቡድኑ ውስጥ የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ለመሙላት እየሞከረ ነው ተብሎ ይታመናል።
ሳፌይዲን መልኩ፣ አካላዊ እንቅስቃሴው እንዲሁም ንግግሩ ከናስረላህ የተቀዳ ነው።
ነገር ግን የናስራላህ ደጋፊም ሆኑ ነቃፊዎች አንደበተ ርቱዑ፣ በተናገረ ቁጥር ሰዎች ዓይናቸውን ከእርሱ እንዳይነቅሉ የሚያደርግ፣ ቅቡልነት ያለው መሪ ለመሆን ሳፌይዲን ምንም ያህል ቢጥር ሊሳካለት አይችልም ይላሉ።
ሳፌይዲን ከናስረላህ ቀጥሎ ሄዝቦላህን እንደሚመራ መወሰኑን የሚገልጽ ነገር እስካሁን ድረስ የተሰማ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ የለም።
በአመራር እርከኑም ሆነ በቡድኑ ውስጥ ከፊት የሚገኝ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ቡድኑን ለመምራትም የተሻለ አማራጭ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ አይታመንም።
የእስራኤል ጥቃት ቡድኑን ማዳከም ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ያለውን ተገዳዳሪ ኃይል አቅም ማጥፋት እና መሪ ሊሆኑ የሚችሉትን ሁሉ መደምሰስ በመሆኑ ሄዝቦላህ በዚህ ጉዳይ ላይ ይፋዊ መግለጫ መስጠት ላይ ጥንቁቅ ሆኗል።












