ሩሲያ ወደ አውሮፓ ጋዝ የሚያስተላልፈውን ዋና መስመር እንደገና ዘጋች

ኖርድ ስትሪም 1 የነዳጅ ማስተላለፊያ  ቧንቧ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሩሲያ ለጥገና በሚል ወደ አውሮፓ የሚሄደውን ኖርድ ስትሪም 1 የተሰኘውን የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧን እንደገና ዘጋች።

በዚህም ለአውሮፓ የሚደርሰው የጋዝ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ቆሟል።

በሩሲያ መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳዳረው ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ጋዝፕሮም ኖርድ ስትሪም የነዳጅ ማስተላለፊያ ላይ የተጣለው ገደብ ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት ይቆያል ብሏል።

ሩሲያ ቀደም ሲልም በቧንቧው በኩል ወደ ውጪ የሚላከውን ጋዝ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሳለች።

በምዕራባውያን አገራት ላይ የኃይል አቅርቦትን እንደ መሳሪያ ተጠቅማለች የሚለውን ክስም ውድቅ አድርጋለች።

የኖርድ ስትሪም የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ከሩሲያ ባሕር ዳርቻ ሴንት ፒተርስበርግ ተነስቶ በባልቲክ ባሕር ስር 1 ሺህ 200 ኪሎሜትር ሸፍኖ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ጀርመን ድረስ የሚዘልቅ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2011 አገልግሎት መስጠት የጀመረው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧው  በቀን ከፍተኛውን 170 ሚሊዮን ኪዪቡክ ሜትር ጋዝ ከሩሲያ ወደ ጀርመንም መላክ ይችላል።

ከዚህ ቀደም ሩሲያ በየዓመቱ ለምታካሂደው የጥገና ሥራ ለአስር ቀናት ዘግታው የነበረ ሲሆን፣ ከተከፈተ በኋላም በ20 በመቶ አቅም ብቻ እየሰራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ ሩሲያ ችግር ያለባቸው መሳሪያዎች ስላሉ ነው ብላለች።

የጀርመን የኔትወርክ ተቆጣጣሪ ፕሬዝዳንት ሩሲያ በሚቀጥሉት ቀናት አቅርቦት ከጀመረች አገሪቱ ባላት ክምችት መቋቋም እንደምትችል ተናግረዋል።

"ችግሩን ለመቋቋም እንደምንችል እገምታለሁ፤ ሩሲያ በመጪው ቅዳሜ ወደ 20 በመቶ መላክ እንደምትጀምር አምናለሁ፤ ነገር ግን ማንም በትክክል ይህንን በእርግጠኛነት መናገር አይችልም" በማለት  ክላውስ ሙለር ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ነገር ግን የጀርመኑ ኢኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሃቤክ ለፋይናንሺያል ታይምስ እንደተናገሩት እርምጃው ከወዲሁ አንዳንድ የጀርመን ኩባንያዎች ምርታቸውን እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል፣ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው ጉዳይ  "አሳዛኝ ነው" ብለዋል።