የመስክ እና የዛከርበርግን የቡጢ ፍልሚያ ጣሊያን ልታስተናግድ ትችላለች ተባለ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS AND GETTY IMAGES
ሁለቱ ጉምቱ የዓለማችን የቴክኖሎጂ አውራዎች ኤለን መስክ እና ማርክ ዛከርበርግ መካከል በፍርግርግ በታጠረ መድረክ ሊካሄድ የታቀደው ፍልሚያ የሮምን ጥንታዊ ገጽታ በሚያሳይ መልኩ በጣሊያን ውስጥ ሊካሄድ ይችላል ተባለ።
የጣሊያን የባህል ሚኒስትር ትርኢቱን በበጎ አድራጎት ዝግጅት መልክ ማዘጋጀትን በተመለከተ ከመስክ ጋር ማውራታቸውን አርብ ዕለት ተናግረዋል።
ቢሊየነሮቹ የቴስላ እና የቀድሞው ፌስቡክ የአሁኑ ሜታ ሥራ አስፈጻሚዎች ከሰኔ ወር ጀምሮ እርስ በርስ ሲጎሻሸሙ ቆይተዋል።
ከውድድሩ መግቢያ ትኬትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዩሮዎች ለሕጻናት ሆስፒታል ይለገሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሆኖም እስካሁን ፍልሚያውን የሚያካሂዱበት ቀን ላይ ከስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን ዛከርበርግ ተናግሯል።
መስክ በቀድሞ ስሙ ትዊተር በሚባለው የማኅበራዊ መድረክ ኤክስ፣ እቅዱን በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም ከባህል ሚኒስትር ጋር መነጋገሩንም ገልጿል።
“ በቦታው ተስማምተናል። በካሜራው ፍሬም የሚገቡት ምስሎችም ጥንታዊቷን ሮምን የሚያሳዩ ሲሆኑ ምንም ዘመናዊ ነገር አይኖርም” ሲል ጽፏል።
ይሁን እንጂ ዋና ከተማዋ ሮም እና በጥንት ጊዜ የግላዲያተር ፍልሚያዎች የተካሄዱበት ታዋቂው ኮሎሲየም ስታዲየም በውድድር ዕይታ ውስጥ አይካተትም ብሏል።
የጣሊያን የባህል ሚኒስትር ጌናሮ ሳንጉሊያንጎ በመግለጫቸው፣ "ይህ ጥሩ የበጎ አድራጎት ዝግጅት ነው ከአገሪቷን ታሪካዊ ጠቀሜታ ጋር የሚስማማ እንዲሁም ባህላዊ ቅርስን የሚጠብቅ ነው" ብለዋል።
“ከመስክ ጋር ዘለግ ያለና የወዳጅነት ንግግር አድርጌያለሁ፤ለጥንታዊቷ ሮም ታሪክ ስላለን ፍቅር ተጨዋውተናል” ብለዋል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።
“ ትልቅ የበጎ አድራጎት ሥራ፣ የተከበረ እና ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ ታሪካዊ ዝግጅት እንዴት ማዘጋጀት እንደምንችል እያሰብን ነበር። . . . በሮም ግን አይካሄድም” ያሉት ሚኒስትሩ፣ በዝግጅቱ ለሁለት የጣሊያን ሕጻናት ሆስፒታሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ ይለገሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ዛከርበርግ የኤክስ ተቀናቃኝ በሆነውና ባለፈው ወር ይፋ በተደረገው ትሬድስ ባሰፈረው ጽሑፍ “ ኤለን ከተፈታነኝ ቀን ጀምሮ ለፍልሚያው ስዘጋጅ ቆይቻለሁ። በቀኑ የምንስማማ ከሆነ ከእኔ ትሰማላችሁ ” ብሏል።
እስከዚያው ድረስ ግን ከእርሱ የምትሰሙት ማንኛውም ነገር የተስማማንበት አለመሆኑን ተረዱ ብሏል።
የ52 ዓመቱ ኤለን መስክ እና የ39 ዓመቱ ማርክ ዛከርበርግ የዓለማችን ዝነኛ የቴክኖሎጂ ቢሊየነሮች ናቸው።
እርስ በርስ የመፋለም ሃሳቡን የጀመረው መስክ በትዊተር ገጹ ላይ ከዛከርበርግ ጋር ለመፋለም ዝግጁ መሆኑን ሰኔ ወር ላይ ከገለጸ በኋላ ነበር።
የሚክስድ ማርሻል አርትስ (ኤምኤምኤ) ሥልጠና ያለው እና በቅርቡ ጁ ጂትሱ ውድድር ላይ ያሸነፈው የሜታ ሥራ አስፈፃሚ ዛከርበርግም ለመስክ የእንጋጠም ጥሪ “ዝም ብለህ አድራሻውን ላክልኝ" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።












