በኮሮና መሞትን ከመፍራት፤ መንግሥታዊ ሰነዶችን ቀዶ መጸዳጃ ቤት እስከ መጣል የደረሱት ዶናልድ ትራምፕ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሴት ልጃቸውን ከሥራ ለማባረር ከጫፍ ደርሰው ነበር። በተደጋጋሚም ሰነዶችን መጸዳጃ ቤት ይጥሉ እንደነበር አዲስ የወጣ መጽሐፍ ይፋ አደረገ።

'ኮንፊደንስ ማን' የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛዋ ማጊ ሃበርማን መጽሐፍ ነው። ከላይ ያሉትን አነጋጋሪ ጉዳዮች እና ሌሎችም የዚህ መጽሐፍ መገለጦች ናቸው። መጽሐፉ ዛሬ ለአንባቢያን ቀርቧል።

በመጽሐፉ ትራምፕ ከኒው ዮርክ ነጋዴ እስከ ፕሬዝዳንትንት እንዲሁም ከዚያም በኋላ እስካለው ህይወታቸው ያትታል።

ትራምፕ ከወዲሁ በመጽሐፉ ላይ ጦርነት ጀምረዋል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብቅ ብለው ሃበርማን “በርካታ የተቀሸቡ ታሪኮችን ሳታጣራ” አቅርባለች ብለዋል።

'ኮንፊደንስ ማን' ይፋ ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል ስምንቱ እነሆ፡

1) ትራምፕ ኢቫንካ እና ጃሬድ ኩሽነርን ማባረር ፈልገው ነበር

ሃበርማን እንደጻፈችው ከሆነ ትራምፕ የወቅቱን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጆን ኬሊን እና የዋይት ሐውስ አማካሪ ዶን ማክጋንን ካገኙ በኋላ አንድ ውሳኔ ሊያሳልፉ ነበር።

በዋይት ሐውስ አማካሪ የነበሩትን ሴት ልጃቸው ኢቫንክን እና የልጃቸውን ባለቤት ጃሬድ ኩሽነርን ሥራቸውን ሊለቁ እንደሆነ በትዊተራቸው ሊያሰፍሩ ከጫፍ ደርሰው ነበር።

ትዊተሩን ከመጻፋቸው በፊት ሁለቱንም እንዲያነጋግሩ ኬሊ መከሯቸው። ትራምፕ ግን አላናገሯቸውም። ሁለቱም በሥራቸው ቀጠሉ።

ትራምፕ ስለ ልጃቸው ባለቤት ያላቸው ግምት አነስተኛ መሆኑን መጽሐፉ አስነብቧል። ኩሽነር በ2017 የሰጠውን መግለጫ ተከትሎም “ልጅ ነገር ነው” ብለዋል ተብሏል።

ትራምፕ ልጃቸውን እና ባሏን ለማባረር ፈልገው ነበር መባሉን አስተባብለዋል። “ይህ ልብ ወለድ ነው። ለአንዴም ያላሳብኩት ጉዳይ ነው” ብለዋል።

2) ትራምፕ በሜክሲኮ ያሉ የአደንዛዥ ዕጽ ቤተ ማምረቻዎችን በቦንብ ሊያፈነዱ አቅደው ነበር

በሜክሲኮ የሚገኙ የአደንዛዥ ዕጽ ቤተ ሙከራዎችን በቦንብ የማፈንዳት ሐሳብ ትራምፕ አንስተዋል። አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ መሆኑን ሃበርማን ጽፋለች። ሃሳቡ የቀድሞውን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ማርክ ኤስፐርን አስደንግጧል።

ትራምፕ በአሜሪካ የሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያ ከሆኑት ብሬት ጊሮይር ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ነው ይህንን ሃሳብ ያነሱት።

ጊሮይር ወደ ፕሬዝዳንቱ ቢሮ የገቡት በጦሩ ውስጥ እንደማገልገላቸው ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ነበር። ሜክሲኮ ውስጥ የአደገኛ ዕጽ ማዕከላትን ዒላማ ማደረግ እና ዝውውሩን መግታት እንደሚያስፈልግ ለትራምፕ ተናግረዋል።

ትራምፕ ተሳሳቱ። ጥያቄው ወታደራዊ መሰላቸው። በቦንብ ይደብደቡ ሲሉም ሃሳብ አቀረቡ። ዋይት በምላሹም ጊሮይር ዩኒፎርሙን እንዳይለብሱ ጠይቀዋቸዋል።

3) ትራምፕ በኮቪድ እሞት ይሆን ሲሉ ሰግተው ነበር

ትራምፕ በ2020 በኮቪድ ተይዘው ነበር። ጤንነታቸው አስጊ ሆኖም ነበር። እንዳይሞቱም ፈርተው ነበር።

በአንድ ወቅትም የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ቶኒ ኦርናቶ ህመማቸው ከተባባሰ መንግሥቱን የሚያስቀጥል ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ለትራምፕ ነግረዋቸዋል።

ወረርሽኙን ለመቋቋም ቢሰሩም ይህ ስጋት አብሯቸው ቆይቷል። ቫይረሱ ስማቸውን እና ፖለቲካውን ሊያበላሸው ይችላል የሚል ስጋትም አሳድሮባቸው ነበር።

የቅርብ አጋሮቻቸውን የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብላቸውን እንዲያወልቁ ወትውተዋል። በወቅቱ የኒው ዮርክ ገዢ የነበሩት አንድሪው ኩሞ ስለቫይረሱ ቲቪ ላይ እንዳይናገሩም መክረዋቸው ነበር።

“ስለዚህ ጉዳይ ብዙ አታውራ። የበለጠ ችግር ታደርገዋለህ” ሲሉ ትራምፕ ለኩሞ መምከራቸውን መጽሐፉ ያትታል።

4) ትራምፕ ስለሃብታቸው ለዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር አንስተዋል

የሃበርማን መጽሃፍ ትራምፕ ከብዙ የዓለም መሪዎች ጋር መገናኘታቸውን ይገልጻል።

ለምሳሌ ከቀድሞዋ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ጋር ተነጋግረዋል። መሪዎቹ ከተነጋገሩበት ጉዳዮች አንዱ ስለ ውርጃ ነበር።

“አንዳንዶች በሕይወት መኖርን ይደግፋሉ። ሌሎች በራስ የመወሰን ነጻነትን ይደግፋሉ። እስቲ አስቢው በንቅሳት የተዥጎረጎረ እንስሳ ልጅሽን ደፍሮ ሲያስረግዛት?” ሲሉ ማብራሪያ መስጠታቸው ተጠቅሷል።

አስከትለውም ትራምፕ ርዕስ ቀየሩ። ትኩረታቸውም ስለሰሜን አየርላንድ ሆነ። እዚያ ባለ የግል ንብረታቸው አካባቢ የሚሠራ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በማንሳት መሠራት የለበትም ሲሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሯ ጋር መነጋገራቸው ተገልጸወል።

5) የተሸነፉበት ምርጫ ውጤት እንዲቀለበስ ያደረጉት ሙከራ

የ2020ውን ምርጫ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደሚያሽንፉ ግልጽ የሆነበት ጊዜ ነው። ትራምፕ ስልክ አንስተው ወደ ቀድሞው የኒው ዮርክ ገዢ እና የግል ጠበቃቸው ሩዲ ጁሊያኒ መደወል ጀመሩ።

ትራምፕ የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች ጋር ደውለዋል። የምርጫውን ውጤት ቀልብሱልኝ ይሉ ነበር። የሌሎቹ አልሳካ ሲል ነው “እሺ ሩዲ አንተ ኃላፊነት አለብህ። ሂድ የፈለከውን አድርግ። ምንም አያስጨንቀንም” በማለት ለጁሊያኒ ተናገሩ።

“ጠበቆቻችን አይረቡም” ማለታቸውን መጽሐፉ አስነብቧል። በተደጋጋሚም የዋይት ሐውስ አማካሪ ፓት ሲፖሎን ወቅሰዋል።

በወቅቱ ትራምፕ በሴራ ጽንሰ ሃሳቦች መጠመዳቸውን መጽሐፉ ጠቅሷል። የራሳቸው ጠበቆች ግራ ገብቷቸዋል በማለትም ሌሎችን እያፈላለጉ ነበር ብሏል መጽሐፉ።

6) ትራምፕ ስለታክስ ጉዳይ ምላሽ የመጠላቸው አውሮፕላን ላይ ነው

በ2016 የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ትራምፕ በአውሮፕላን እየተጓዙ ነበር። የምርጫ ቅስቀሳ ሥራ አስኪያጃቸው ኮሪ ሌዋንዶውስኪ እና ቃል አቀባያቸው ሆፕ ሂክስ ስለ ታክስ ጉዳያቸው እንዲያብራሩ ተጠየቁ። ጉዳዩ የምርጫ ጉዟቸውን ያሰናክላል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ነው።

ትራምፕ ወንበራቸው ላይ ወደ ኋላ ተለጥጠው ቁጭ ካሉ በኋላ በፍጥነት አንድ ሃሳብ መጣላቸው። “እንደምታውቁት የእኔ ታክስ ጉዳይ ሁሌም ኦዲት እንደተደረገ ነው። ሁሌም ኦዲት እደረጋለሁ” ሲሉ መለሱ።

“ስለዚህም ምን እያልኩ መሰላችሁ ‘ኦዲት በማልደረግበት ወቅት ይፋ አደርገዋለሁ’ እላለሁ። ‘ምክንያቱም ሁሌም ኦዲት እደርጋለሁ።’”

ከሪቻርድ ኒክሰን ጀምሮ ሁሉም የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በፈቃደኝነት የታክስ መረጃቸውን ይፋ ያደርጋሉ። በ2020 ኒው ዮርክ ታይስ አንድ መረጃ ይዞ ወጣ። ትራምፕ ፕሬዝዳንት በሆኑበት ዓመት 750 ዶላር ብቻ ነው ታክስ የከፈሉት ብሏል በጽሑፉ።

7) ትራምፕ መረጃዎችን መጸዳጃ ቤት ይከቱ ነበር

ትራምፕ ዋይት ሐውስ እያሉ መጸዳጃ ቤት በተደጋጋሚ ይደፈን ነበር። መጸዳጃ ቤቶቹ በታተሙ ወረቀቶች የሚደፈኑት ትራምፕ በሚጥሉት ወረቀት እንደሆነ የዋይት ሐውስ ሠራተኞች ያምናሉ።

በተደጋጋሚም ፕሬዝዳንት መረጃ ሕግን በመጻረር ወረቀቶችን ይቀዱ ነበር ተብለው ይከሰሳሉ። በሕጉ መሠረት ፕሬዝዳንቱ ያገኙት ወይም ያዘጋጁት መረጃ የአገሪቱ ንብረት ነው። ፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን ሲጠናቀቅም ለአሜሪካ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ይሰጣል ይላል።

እነዚህ ጉዳዮች መውጣት ጀመሩት ቤተ መዛግቡት ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ሰነዶቹን አለማግኘቱን ካስታወቀ በኋላ ነው።

ትራም ፍሎሪዳ የሚገኝ ቤት አላቸው። ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ በዚህ ቤት መዛግበቶችን አስቀምጠዋል በሚል የአገሪቱ የፍትህ መሥሪያ ቤት ወንጀል ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።

8) ትራምፕ የአናሳ ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ሠራተኞች አስተናጋጅ እንደሆኑ ያስቡ ነበር

ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን ከተቆናጠጡ በኋላ አንድ ኮንግረስ ስብሰባ አካሂደዋል ይላል የሃበርማን መጽሐፍ።

በዚሁ ወቅት አናሳ ቁጥር ካላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የመጡ ዴሞክራት ሠራተኞች አስተናጋጅ ስለመሰሏቸው እንዲያስተናግዷቸው ጠይቀዋል።

በመጽሐፉ እንደተገለጸው ትራምፕ ጥያቄውን ያቀረቡት ለሴናተር ቻክ ሹመር እና ለአፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ነበር።

ትራምፕ ሌላም ማንነት ተኮር አስተያየት መስጠታቸውን መጽፉ አስነብቧል።