በሩሲያ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ 11 ሰልጣኝ ወታደሮች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሩሲያ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ላይ ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት 11 ሰልጣኝ ወታደሮች ተገደሉ።
በዩክሬን ለመዋጋት ፈቃደኛ በሆኑ ሰልጣኝ ወታደሮች ላይ ሁለት ታጣቂዎች ተኩስ እንደከፈቱ የመንግሥት የዜና ወኪል ሪያ ዘግቧል።
ሰልጣኝ ወታደሮቹ በወቅቱ የጦር መሳሪያ ስልጠና እየወሰዱም ነበር ተብሏል።
ጥቃቱን ያደረሱት ግለሰቦች ከቀድሞዋ የሶቭየት ሪፐብሊክ የመጡ ናቸው በማለት የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ከመግለጽ ውጭ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ዩክሬንና ሩሲያ በሚዋሰኑበት ቤልጎርግ ግዛትም በነበረው የተኩስ ልውውጥ ግለሰቦቹ ተገድለዋል።
ተጨማሪ 15 ሰዎች ቆስለዋል።
“በዩክሬን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ምልምሎች የጦር መሳሪያ ልምምድ ላይ በነበሩበት ወቅት አሸባሪዎች ተኩስ ከፍተዋል “ በማለት ሪያ የመከላከያ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
“በዚህም የተኩስ ልውውጥ 11 ሰዎች ሞተዋል። ተጨማሪ 15 ሰዎች ደግሞ ቆስለው ወደ ህክምና ተቋም ተወስደዋል” ብሏል።
የቤልጎሮድ ግዛት አስተዳዳሪ በበኩላቸው የተገደለም ሆነ የተጎዳ የከተማዋ ነዋሪ የለም ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፈው ወር የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ ቀደም ወታደራዊ ስልጠናዎችን የወሰዱ 300 ሺህ ሩሲያውያን እንዲከቱ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ይህ ትዕዛዝ በመላው ሩሲያ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን በርካቶች ሃገሪቷን ለቀው ለመውጣት እየሞከሩ ይገኛሉ።
የክተት አዋጁ ከተጠራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በሳይቤሪያ በሚገኝ የምዝገባ ቢሮ አንድ ወታደራዊ መልማይ በጥይት ተመትቷል።
ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት ፑቲን ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች መክተታቸውን እና ተጨማሪ ቅስቀሳ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።












