ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ ፖሊስ በምትጠበቀው ሄይቲ ወሮበሎች ባደረሱት ጥቃት 20 ሰዎች ተገደሉ
የታጠቁ የሄይቲ ወሮበሎች በአንዲት አነስተኛ ከተማ ባደረሱት ጥቃት ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ።
ግራን ግሪፍ የተሰኘው የወሮበሎች ቡድን ነው ጥቃቱን የፈፀመው። 50 ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።
የታጠቁ ወሮበሎች ጥቃት የፈፀሙባት ፖንት ሶንዴ ከተማ ከመዲናዋ ፖርት-አው-ፕሪንስ 71 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች የአካባቢው ሰዎች በሞተር ብስክሌት እና በእግራቸው ሲሸሹ አሳይተዋል። አንድ አቃቤ ሕግ ጥቃቱን “ጅምላ ጭፍጨፋ” ብለውታል ሲል ኦሰሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የታጠቁ ወሮበሎች አብዛኛውን የሄይቲ ክፍል የተቆጣጠሩት ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት የሚመራው የሰላም አስከባሪ በሥፍራው ይገኛል።
የኬንያ የፖሊስ መኮንኖች ባለፈው ሰኔ ወደ ሥፍራው አቅንተው በሀገሪቱ መረጋጋት እንዲመጣ እየሠሩ ይገኛሉ።
በጥቃቱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር እስካሁን በውል አይታወቅም። የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የሟቾች ቁጥር ከ50 ይበልጣል ሲሉ ዘግበዋል።
አንድ የሄይቲ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ደግሞ የሟቾች ቁጥር 20 አሊያም ከዚያ በላይ ሊሆን ይችላል ማለቱን ኤፒ አስነብቧል።
ግራን ግሪፍ የተባለው የታጠቁ ወሮበሎች ቡድን ሄይቲ ውስጥ ካሉ እጅግ አመፀኛ ቡድኖች አንዱ ነው። በአውሮፓውያኑ 2023 ጥር ወር ላይ የዚህ ቡድን አባላት በፖርት ሶንዴ ፖሊስ ጣቢያ ጥቃት ፈፅመው ስድስት የፖሊስ መኮንኖች ገድለዋል ተብለው ይወቀሳሉ።
ቡድኑ 700 ሺህ ሕዝብ የሚጠቀመውን ሆስፒታል አስዝግቷል የሚል ወቀሳም ይቀርብበታል።
100 ገደማ አባላት ያሉት ይህ የታጣቂ ወሮበሎች ቡድን በግድያ፣ መድፈር፣ ዘረፋ እና አፈና ወንጀሎች ይፈለጋል ሲል ኤፒ የተባበሩት መንግሥታትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የቡድኑ መሥራች እና የወቅቱ የቡድኑ መሪ የሆኑ ግለሰቦች በዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል ሰዎች ናቸው።
ሐሙስ ዕለት የተፈፀመው ጥቃት የሄይቲ ባለሥልጣናት በመላው ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካወጁ ከአንድ ወር በኋላ የተከሰተ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጌሪ ኮናይል ታጣቂ የወንበዴ ቡድኖችን ለማጥፋት ቃል የገቡ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ደግሞ “ኃይል መጠቀም ግዴታ ነው” ይላል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ 2500 ፖሊሶች ወደ ሄይቲ እንዲያቀኑ የሚለውን ሐሳብ ያፀደቀ ሲሆን ኬንያ በጠቅላላው 1000 ፖሊሶች ትልካለች።
የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ጥር ባወጣው መረጃ መሠረት ባለፈው ዓመት የሄይቲ ታጣቂ ወሮበሎች በፈፀሙት ጥቃት 8400 ሰዎች ተገድለዋል።