ሲሪላንካ ወሳኝ ላልሆኑ አገልግሎቶች ነዳጅ መሸጥ አቆመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአስር ዓመታት ውስጥ እጅግ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ እያጋጠማት የምትገኘው ሲሪላንካ ወሳኝ ላልሆኑ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ መሸጥን አቁማለች።
በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ለህክምና አገልግሎት እና ምግብ ለማጓጓዝ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች፣ አውቶቡሶች፣ ባቡሮች እና ተሽከርካሪዎች ብቻ ነዳጅ እንዲሞሉ ተፈቅዶላቸዋል።
መንግሥት በከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ያደረገ ሲሆን፣ የአገሪቱ 22 ሚሊዮን ነዋሪዎች ከቤት እንዲሠሩ በባለሥልጣናት ተነግሯቸዋል።
የደቡብ እስያዋ አገር እንደ ነዳጅ እና ምግብ ያሉ ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችላትን ገንዘብ ለማግኘት እየተነጋገረች ነው።
“በ1970ዎቹ የነዳጅ ቀውስ ተፈጥሮ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ያለውን ፍላጎት ለመቀነስ የተሽከርካሪዎች የፍጥነት ገደብ እና የኮታ አቅርቦት ከተዋወቀ ወዲህ ስሪላንካ ለተራው ሰው የነዳጅ ሽያጭን በማስቆም ከባድ እርምጃ የወሰደች የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች” ሲሉ በኢንቨስቴክ የጋዝና ነዳጅ ምርምር ኃላፊው ናታን ፓይፐር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እገዳው በሲሪላንካ ያለውን ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት ውስን መሆኑን በግልጽ አሳይቷል።
ብዙዎቹ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ያለ ነዳጅ ኑሯቸውን እንዴት እንደሚገፉ ግራ ተጋብተዋል። ለወራት በስሪላንካ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ረዣዥም ሰልፎች ይታዩ ነበር።
በዋና ከተማዋ ኮሎምቦ የታክሲ አሸከርካሪ የሆነው የ29 ዓመቱ ቺንታካ ኩማራ እገዳው “በሰዎች ላይ የበለጠ ችግር ይፈጥራል” ብሎ ያስባል።
ለቢቢሲ ሃሳቡን ሲገልጽ “እኔ የቀን ደሞዝተኛ ነኝ። ወረፋ ይዤ ለሦስት ቀናት ቆይቻለሁ። መቼ ቤንዚን እንደማገኝ አላውቅም" ብሏል።
አሽከርካሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ የተነገረ ሲሆን የቀረ የነዳጅ ክምች ካለ ይከፋፈላል በሚል ቁጥር ተሰጥቷቸዋል። አንዳንዶቹ መሰለፋቸውን ቢቀጥሉም ሌሎች ግን ተመልሰዋል።
የ52 ዓመቱ ኤስ ዊጄቱንጋ በበኩላቸው "ለሁለት ቀናት ወረፋ ይዤ ነበር። 11 ቁጥር ተሰጥቶኛል ግን ነዳጅ መቼ እንደምወስድ አላውቅም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አሁን ወደ ሥራ መሄድ ስላለብኝ ተሽከርካሪዬን እዚህ ትቼ በባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ከመሄድ ውጪ ምንም አማራጭ የለኝም" ብለዋል።
ኮሎምቦ ውስጥ ኮታሄና በሚባለው መንደር ባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪ ያለው ኬናት እንደ እሱ ያሉ ሰዎች “ይበልጥ መጎዳታቸውን” ገልጿል።
"ቤተሰባችን በቀን ሦስት ጊዜ ይመገብ ነበር። አሁን የምንበላው በቀን ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ አንድ ጊዜ ወደ መብላት ይወርዳል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ"
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት የኢኮኖሚ ቀውስ ሌላ የነደዳጅ ዋጋ መጨመር እና የታክስ ቅነሳ መደረጋቸው ተደማምረው ስሪላንካ አስፈላጊ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስችላትን በቂ የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ምክንያት ሆኗል።
ከፍተኛ የነዳጅ፣ የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት የአገሪቱን የኑሮ ውድነት እንዲንር አድርጎታል። ብዙዎች ገቢያቸውን ከግል ሞተር ሳይክሎቻቸው ያገኛሉ።
ሰኞ ዕለት የአገሪቱ መንግሥት እስከ ሐምሌ 10 ድረስ የግል ተሽከርካሪዎች ቤንዚን እና ናፍታ እንዳይገዙ እንደሚከለክል ተናግሯል።
የአገሪቱ ካቢኔ ቃል አቀባይ ባንዱላ ጉኔዋርዴና በበኩላቸው ስሪላንካ “በታሪኳ እንደዚህ ያለ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ገጥሟት አያውቅም” ብለዋል።
በገንዘብ ችግር የተሸበሸበችው አገር ርካሽ የነዳጅ አቅርቦት ለማግኘት ባለሥልጣናትን ወደ ነዳጅ አምራቾቹ ሩሲያ እና ኳታር ልካለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሳምንቱ መጨረሻ ባለሥልጣናቱ እንዳስታወቁት፣ በአገሪቱ በመጪዎቹ ቀናት አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል 9,000 ቶን ናፍጣ እና 6,000 ቶን ቤንዚን ብቻ ነው ያለው።
ክምችቱ በመደበኛ መንገድ ከተሰራጨ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚያልቅ ተገምቷል.
የኃይል እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ካንቻና ዊጄሴኬራ እሑድ ዕለት ለጋዜጠኞች “ተጨማሪ ክምችት ለማግኘት የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው። ይህ መቼ እንደሚሆን ግን አናውቅም” ሲሉ ተናግረዋል።
አገሪቱ በግንቦት ወር በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም አቀፍ አበዳሪዎች መክፈል ያለባትን ዕዳ ሳትከፍል ቀርታለች።
ይህም በፕሬዚዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ መንግሥት ላይ ለሳምንታት የዘለቀውን ተቃውሞ ተከትሎ የተፈጠረ ነበር።
የፕሬዝዳንቱ ወንድም ማሂንዳ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ ለቀዋል። ፕሬዝዳንቱ አሁንም ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ነው።
በዋና ከተማው ነዳጅ ለመግዛት የሚጠባበቀው ካናን የተባለ አሸክርካሪ “መንግሥት ምንም ዓይነት እርምጃ የሚወሰድ አይመስልም” ሲል ለቢቢሲ ታሚል ተናግሯል።
“እንድንታገስ እየጠየቁን ነው። ዶላር የለንም ይላሉ። እኔ ግን ለዚህ ተጠያቂው ማነው? ስል መንግሥትን እጠይቃለሁ” ብሏል።
በምትኩ "የተማሩ ወጣቶች" አገሪቱን መምራት እንዳለባቸው ጠቁሟል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቡድን በሦስት ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ስምምነት ላይ ለመነጋገር ወደ ሲሪላንካ አቅንቶ ነበር።
መንግሥትም አስፈላጊ እቃዎች ለማስገባት ከሕንድ እና ቻይና እርዳታ እየጠየቀ ነው።
አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ራኒል ዊክሬሜሲንጌ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንደገለጹት እንደ ምግብ፣ ነዳጅ እና ማዳበሪያ ላሉ አስፈላጊ ዕቃዎች ለመክፈል አገሪቱ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ቢያንስ 5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል።
የምግብ እጥረት ሊከሰት ይችላል በሚልም ባለፉት ሳምንታት ሚኒስትሮች ገበሬዎች ብዙ ሩዝ እንዲያመርቱ ጠይቀዋል።
መንግሥት በሲሪላንካ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከሚያስገኙት አንዱ የሆነው የቱሪስት ዘርፍ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መጎዳቱን ለቀውሱ ተጠያቂ አድርጓል።
ብዙ ባለሙያዎች ግን የመልካም አስተዳደር እጦት ለኢኮኖሚው ውድቀት ዋነኛው መንስኤ ነው ይላሉ።












