የዩክሬን የባሕር ላይ ድሮን በሩሲያ የባሕር ኃይል መርከብ ላይ ጥቃት ፈጸመ

የባሕር ድሮን

የፎቶው ባለመብት, RYBAR

ታትሟል

የሩሲያ ባሕር ኃይል መርከብ በጥቁር ባሕር ላይ በዩክሬን የባሕር ድሮን ጥቃት እንደተፈጸመበት የዩክሬን ምንጮች ገለጹ።

በሩሲያው ጥቁር ባሕር ጠረፍ ኖቮሮሲይስክ አውራጃ ሑመስ ሌሊት ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱ ተዘግቧል።

አርብ ዕለት ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተሰራጩ ምስሎች እንደሚያሳዩት የሩሲያ የውጭ ንግድ ቀጣና በሆነው በዚህ የባሕር ዳርቻ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ተሰምቷል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው ከዩክሬን የተቃጡ ሁለት የባሕር ድሮን ጥቃቶችን መክቷል።

ሚኒስቴሩ አክሎ ድሮኖቹ አደጋ ከማድረሳቸው በፊት በአካባቢው ያለው የባሕር ኃይል መቀመጫ ጥቃቱን ማምከኑን ገልጧል።

ጥቃቱን ተከትሎ የባሕር ዳርቻው ለጊዜው ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በሥፍራው እንዳይካሄድ እንደታገደ ነዳጅ የሚጭነው ካስፒያን ፓይፕላይን ኮንሶርቲየም የተባለ ኩባንያ አሳውቋል።

የባሕር ድሮኖች መጠናቸው ያነሰ ሰው አልባ ጀልባዎች ሲሆኑ ውሃ ላይ አሊያም ሰርገው በመግባት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

'ቢቢሲ ቬሪፋይ' ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው ዩክሬን ቢያንስ 10 የባሕር ድሮን ጥቃቶች ያደረሰች ሲሆን፣ የብዙዎቹ ዒላማዎች የሩሲያ ወታደራዊ መርከቦች እና የባሕር ኃይል መቀመጫዎች ናቸው።

ከዚህ ቀደም ዩክሬን ባደረገችው ጥቃት ሴቫስቶፖል እና ኖቮሮሲይስክ የተሰኙ ቦታዎች የሚገኙ የሩሲያ መርከቦችን ዒላማ አድርጋለች።

ይህ መረጃ የተገኘው የሩሲያ እና ዩክሬን ባለሥልጣናት ከሰጡት መግለጫ እና የአገራቱ መገናኛ ብዙኃን ከዘገቡት ነው።

የዩክሬን መከላካይ ሠራዊት የዜና ምንጮች፤ ባለፈው ሐምሌ በኬርች ድልድይ ላይ በደረሰው ጥቃት የባሕር ድሮኖች ጥቅም ላይ እንደዋሉ ለሲኤኤን ተናግረዋል።

ኖቮሮሲይስክ በጥቁር ባሕር ዳርቻ ከሚገኙ ጠረፎች ትልቁ ነው።

ፍንዳታው ከተሰማ በኋላ የደኅንነት አገልግሎቶች ጥቆማ እንደደረሳቸው በሥፍራው የሚገኙ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አረጋግጠዋል ሲል የሩሲያ ብሔራዊ ጣቢያ ዘግቧል።

ዩክሬን እስካሁን ስለደረሰው ጥቃት ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።

ሩሲያ፤ በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት ከዩክሬን ጋር ከተደረሰው እህል በባሕር በኩል እንዲተላለፍ ከሚፈቅደው ስምምነት ከወጣች በኋላ ባሉት ሳምንታት የባሕር ላይ ጥቃቶች በርክተዋል።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሩሲያ በጥቁር ባሕር ዳርቻ በሚገኘው የኦዴሳ እና ቾርኖኮርስክ ጠረፍ ላይ ጥቃት ያደረሰች ሲሆን፣ ባለሥልጣናት 60 ሺህ ቶን ገደማ እህል ከጥቅም ውጭ ሆኗል ይላሉ።

በሌላ ዜና ሩሲያ ዛሬ አርብ ዕለት 10 የዩክሬን በራሪ ድሮኖችን ክሬሚያ ላይ መትታ መጣሏን ተናግራለች።