ለአውሮፓ የእግር ኳስ ከዋክብት ቅንጡ ድግስ የሚያዘጋጁት ሦስቱ ጓደኛሞች
![ኢማኑዔል [ከግራ] እና ዋርድ [ከቀኝ ሁለተኛ] ለጁቬንቱሱ ዌስተን ማኬኒ እና ለሻልከው ራቢ ማቶንዶ ጋር ሰርተዋል](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/93f6/live/80fe7170-fdcb-11ec-bfa6-89ae37be3a04.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, AMSLUX
የጁቬንቱሱ አጥቂ ዱሳን ቭላሆቪች በዋትስአፕ ቁጥርዎ አርብ ደውሎ ለቅዳሜ የግል አውሮፕላን እፈልጋለሁ ብሎ ሲጠይቅ ያስቡት።
ይህ የሦስቱ ጓደኛሞች የዕለተለት ኑሮ ነው።
ሦስቱ ወጣት ጓደኛሞች ለአውሮፓ ኮከብና ሀብታም እግር ኳሰኞች ድግስ ማሰናዳት ነው ሥራቸው።
ለቭላሆቪችና ጓደኞቹ አውሮፕላን አዘጋጅተው የድግስ ዓለም ወደምትባለው የስፔኗ ደሴት ኢቢዛ መሸኘት አለባቸው።
የ26 ዓመቱ ኢማኑዔል፣ የ24 ዓመቱ ሚቼልና የ23 ዓመቱ ዋርድ ለእግር ከዋክብት ቅንጡ ድግስ የሚያሰናዳ ድርጅት አላቸው።
አምስላክስ አውሮፓ ውስጥ ለታዋቂ እግር ኳሰ ተጫዋቾች ቅንጦት ከሚያመቻቹ ድርጅቶች መካከል ቀንደኛው ነው።
ዓላማቸው አንድና አንድ ነው - የእግር ከዋክብቱ የሚጠይቅቱን ነገር ሁሉ ሟሟላት።
125 ሺህ ፓውንድ የሚያወጣ የእጅ ሰዓት? አሊያም 20 ሺህ ፓውንድ የሚጠይቅ ቦርሳ? ወይ ደግሞ 10 ሺህ ፓውንድ የተተመነለት አዲስ የጂም ጫማ? ምንም ችግር የለውም።
ይህ ለሦስቱ ጓደኛሞቹ የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይደለም። ሥራቸው ነውና።
ጓደኛሞቹ ከሦስት ዓመት በፊት ነው መኖሪያቸው በሆነችው አምስተርዳም ሳሉ ነው ይህ ሐሳብ ብልጭ ያለላቸው።
በወቅቱ ኢማኑዔል የጥሪ ማዕከል ሠራተኛ ነበር፤ ዋርድና ሚቼል ደግሞ ጂምናስቲክ አሠልጣኝ ነበሩ።
ነገር ግን ሦስቱም በእግር ኳስ ፍቅር ያበዱ ናቸው። በዲዛይነር ለሚሰፉ አልባሳት ያላቸውም ፍቅር ለየት ያለ ነው።
ጓደኛሞቹ አዲስና ብርቅዬ የሚባሉ የጂም ጫማዎችና አልባሳት የት እንደሚገኙ ጠንቅቀው ያውቃሉ።
አንድ ማለዳ በዘመናይ ፋሽን አለባበሱ ለሚታወቀው ቱርካዊው የክንፍ ተጫዋች ቢላል ባሳሺኮግሉ የኢንስታግራም መልዕክት ይልኩለታል።
መልዕክቱ እንዲህ ይላል “በኢንስታግራም ገፅህ ማስታወቂያ የምትሠራልን ከሆነ በጣም ውድ የሆነ ጫማ እናቀርብልሃለን።”
ቢላል ተስማማ፤ ጓደኛሞቹም ቢዝነሳቸው ተመነደገ።
ሌሎች ተጫዋቾች መግተልተል ጀመሩ። ስምምነቱ ተመሳሳይ ነው። እነሱ ጫማና አልባሳት ያቀርባሉ፤ ተጫዋቾቹ ደግሞ በማኅበራዊ ገፆቻቸው ያስተዋውቋቸዋል።
ኔዘርላንድ ውስጥ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች አልፎ የጣሊያን ሴሪ አ ከዋክብት የመልዕክት ሳንዱቃቸውን ያንኳኩ ጀመር።
አሌሳንድሮ ባስቶኒ፣ ፌዴሪኮ ኪዬዛ፣ ዌስሊ ፎፋና. . . ሌሎችም የአውሮፓ እግር ኳስ ከዋክብት መምጣት ያዙ።
ከተጫዋቾቹ አልፎ የከዋክብቱ ሚስቶች አንድ ነገር ሲፈልጉ ለሦስቱ ጓደኛሞች ስልክ መምታት ጀመሩ።
ኢማኑዔል፣ ዋርድና ሚቼል አሁን ከ100 በላይ ተጫዋቾችን በደንበኝነት ይዘዋል።
ሦስቱ ባልንጀሮች ጫማና ልብስ ከማቅረብ አሊያም የፋሽን ምርቶችን ከማጋዘት ያለፈ ሥራ መሥራት ፈለጉ።
“ለተጫዋቾቹ ሦስት ነገር ነው የምናቀርበው - ጊዜ፣ ዕውቀትና እምነት። የሚፈልጉትን የትኛውም ነገር በማቅረብ ጊዜያቸውን እንቆጥባለን” ይላል ኢማኑዔል።
“ይህ ብቻ አይደለም፤ ምን ዓይነት ፋሽን ቢከተሉ እንደሚሻል ምክር እንሰጣለን። በእኛ እምነት እንዲኖራቸው እናደርጋለን።ከፋሽን ባለፈ የእረፍት ቀናቸውን የሚያሳይልፉበት ቦታ፣ የእጅ ሰዓት፣ ግል አውሮፕላን፣ ፓርቲ እንድናዘጋጅላቸው ይጠይቁን ጀመር።”
በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ ከቤታቸው መውጣት ስለማይችሉ የፈለጉትን ነገር የሚያርቡላቸው እነሱ ነበሩ።
ጓደኛሞቹ ደንበኞቻቸውን ወደ ቅንጡዎቹ የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያዎች ኢቢዛና ማያሚ ወስደው ይመልሳሉ።
“ደንበኞቻችን [ከዋክብቱ] ትኩረታቸው ሜዳ ላይ ብቻ እንዲሆን ነው የምንፈልገው” ይላል ኢማን።
ሦስቱ ሥራ ፈጣሪዎች አሁን የድሮ ሥራቸውን እርግፍ አድርገው ትተው ሰጥ ለጥ ብለው የእግር ኳስ ከዋክብትን ቅንጡ ሕይወት ያስተዳድራሉ።
እርግጥ ነው ይህ አዲሱ ሕይወታቸው ብዙ አስገራሚ ነገር እንዲያዩም ምክንያት ሆኗቸዋል።
“አንድ ተጫዋች ‘ለቫለንታይን ዴይ’ አበባ እንድናደርስለት ጠየቀን። ‘በእኛ ይሁንብህ’ ብለን አድራሻ እንዲልክልን ስንጠይቀው የአራት የተለያዩ ሴቶችን አድራሻ ላከልን።”
አድራሻዎቹ በአራት የተለያዩ አገራት የሚገኙ ሴቶች ነበር። እነሱም ሥራቸውን በአግባቡ ከውነው የታዘዙትን አደረሱ፤ “ትዕዛዙን የሰጠን ተጫዋችም፣ አበባው ተላከላቸው ሴቶችም በጣም ተደስተው ነበር” ይላሉ።












