ሌላው ረዥም ኢትዮጵያዊ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ውስጥ ተገኘ

አወሉ ቡጡላ
ታትሟል

በቁመት ረዥም የሆነው አወሉ ቡጡላ ተወልዶ ያደገው በምሥራቅ ጉጂ ዞን ጎሮ ዶላ ወረዳ ነው። 

ከአርብቶ አደር ቤተሰብ የተገኘው አወሉ፣ አሁን የ24 ዓመት ወጣት ነው።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው አወሉ፣ የአባቱን ከብቶች ወርሶ፣ እየነገደ ኑሮውን ይመራል።

አወሉ ቁመቱ እየጨመረ፣ እኩዮቹን እየበለጠ መምጣቱን ያወቀው የ15 ዓመት ጎረምሳ እያለ መሆኑን ያስታውሳል።

“እኔ በልጅነቴ ከብቶችን ስጠብቅ ነው ያደግኩት። በኋላም ትምህርት ቤት ገብቼ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተማርኩኝ። የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ስለሆንኩኝ አባቴ ትምህርት አቁምና ከብቶቼን ውረስ ስላለኝ ወደ ቤት ተመልሼ ትዳር መሰረትኩ” ይላል።

አወሉ በአሁኑ ወቅት ከሻኪሶ አዲስ አበባ እየተመላለሰ ማዕድን እና እንስሳትንም ይነግዳል።

ከዚህ በፊት የረዥም ቁመት ባለፀጋ በመሆኑ አንድም ቀን ተደስቶ እንደማያውቅ የሚናገረው አወሉ፣ ሰዎች እያዩት ይስቁ፣ ከዚህም ሲገፋ አብረውት ፎቶ ለመነሳት ያስቆሙት ነበር።

ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ በቁመት አቻውን አግኝቶ፣ በትይዩ ዐይን ዐይኑን እያየ የልቡን ማውጋት አጥብቆ እንደሚናፍቅ ተናግሯል።

"ከሸኪሶ እኔ ለሥራ ስወጣ ሰው እያየኝ ይስቃል። ሌሎች ደግሞ እያስቆሙኝ አብረውኝ ፎቶ ይነሳሉ። በዚህ የተነሳ ቁመቴን እጠላው ነበር።"

አሁን ግን ቢቢሲ እና ሌሎች የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደሱ ቁመታሞቹን ነገዎ እና አቶ ብርሄን አቅርበው ሲመለከት ራሱን ከእነርሱ ጋር አወዳድሮ ማየት ጀመረ።

ለረዥም ዓመታት እኩዮቹን እንዲሁም ታላላቆቹን ዝቅ ብሎ ያይ የነበረው አወሉ፣ ዛሬ ነገዎን አግኝቶ ዐይን ለዐይን እየተያየ ማውራት ይፈልጋል።

እድሜው 24 መሆኑን የሚናገረው አወሉ፣ "ቁመቱ 2 ሜትር ከ35 ሴሜ ነው" ሲል ከቢቢሲ ጋር በነበረው የስልክ ቃለ ምልልስ ወቅት ተናግሯል።

ከዚህ በፊት ቢቢሲ ያነጋገረው እና ነዋሪነቱ በመቂ የሆነው የ24 ዓመቱ ነገዎ ጂማ 2፡25 ሴሜትር ይረዝማል።

ሌላው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ረዥም ሰው ደግሞ፣ ከአማራ ክልል አዲስ ቅዳም የተገኙ ሲሆን፣ አቶ ብርሄ ጋሹ ይባላሉ።

አቶ ብርሄ ጋሹ፣ ከነገዎ ጂማ ጋር በተገናኙበት ወቅት በቁመት ነገዎ በልጦ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አወሉ ረዥም ብቻ አይደለም። በክብደቱም ገዘፍ ያለ ነው።

አሁን 125 ኪሎ እንደሚመዝን የሚናገረው አወሉ፣ ቁመቱም ክብደቱም እየጨመሩ መሆናቸውን ይናገራል።

ስለ ነገዎ ጂማ ሰምቶ እንደሆን የተጠየቀው አወሉ፣ “ይህ ርዝመት ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አስቤ ስለማላውቅ፣ ራሴን ወደ ማስተዋወቅ፣ ብዙ ፍላጎት አልነበረኝም” በማለት በቴሌቪዥን እንዳየው እና በአካል አለመገናኘታቸውን ገልጿል።

"እኔ በዚህ ቁመት እውቅና አግኝቼ፣ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ ስለማላስብ ወደ ሚዲያ ቀርቤ አላውቅም" የሚለው አወሉ፣ ነገዎ እውቅና ካገኘ በኋላ በዙሪያው ያሉ ሰዎች 'ሂድና ተለካ፤ ክብረ ወሰኑ ያንተ ይሆናል' ስላሉት አዲስ አበባ በሄደበት ወቅት ቁመቱን መለካቱን ይናገራል።

አወሉ ከቦታ ቦታ ለንግድም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ሲንቀሳቀስ ትራንስፖርት መጠቀም ያዳግተዋል።

ወይ ጉልበቱ ረዝሞ ይቸገራል ካልሆነም የመኪናው ጣርያ ጭንቅላቱን ስለሚነካው ያስጎነብሰዋል።

"አንዳንድ ጊዜ ሾፌሮች ቦታ ትይዛለህ በማለት እኔን ለመጫን ፍላጎት የላቸውም፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሁለት ሰውም ቢሆን ከፍዬ እሳፈራለሁ፥"

ይህ የ24 ዓመት ወጣት “እኔ ነገዎ ጂማን በ10 ሴንቲ ሜትር ስለምበልጠው ኢትዮጵያ ውስጥ በቁመት አንደኛ እኔ ነኝ" በማለት በልበ ሙሉነትይናገራል።

በነገዎ ተይዞ ያለው ክብረ ወሰን ወደ ራሱ ለማዞር በማሰብም ወደ አፍሪካ ድንቃ ድንቅ መዝገብ እንደሄደ እና በቅርብ ይህንኑ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት እንደሚያገኝ ተስፋ እያደረገ ነው።

አወሉ የሚኖረው ለኬንያ ድንበር ቅርብ በሆነ አካባቢ በመሆኑ ለእግሩ መጫሚያ በልኩ ለማግኘት አልተቸገረም።

50 ቁጥር ጫማ እንደሚጫማ የሚናገረው አወሉ፣ ዋጋው ከመጨመር ውጪ ጫማ አጥቶ ተቸግሮ እንደማያውቅ ይናገራል።

አወሉ

"ነገዎን አግኝቼው ዐይኑን እያየሁ ማውራት እፈልጋለሁ"

ከምሥራቅ ጉጂ ዞን ጎሮ ዶላ ወረዳ የተገኘው ረዥሙ ወጣት፣ አወል ቡጡላ፣ ረዥም ከሆነው የቁመት አቻው ነገዎ ጂማ ጋር በአካል ተገናኝቶ ማውራት ይፈልጋል።

“ነገዎ የኢትዮጵያ ልጅ ነው እወደዋለሁ፤ እኔ እና እርሱ በቁመት እንቀራረባለን። እርሱን በአካል አግኝቼው ዐይን ለዐይን እየተያየን ለማውራት ያለኝ ፍላጎት ይወጣልኛል፤ ሁሉንም ሰው ወደ ታች እያየሁ ነው የማወራው። ትልቅ ሰው በሚሆንበት ጊዜም ይከብደኛል። ከእርሱ ጋር ግን ፊት ለፊት እየተያየን እንጨዋወታለን።"

ቁመቱ እና ክብደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የሚናገረው አወሉ፣ ለወደፊትም ከዚህ በላይ ልጨምር እችላለሁ ሲል ይናገራል።

ከቤተሰቡ ውስጥ ብቸኛው ረዥም መሆኑን እና ጎረቤቶች እና ቤተሰቡ ይህንን ቁመቱን የፈጣሪ ስጦታ ነው ብሎ አንደሚወዱለትም ገልጿል ።