ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ነዋሪዎች አተኩረው በመመልከት አጫሾችን እንዲያስቆሙ የሆንግ ኮንግ የጤና ባለሥልጣን አሳሰቡ
የሆንግ ኮንግ ከተማ የጤና ባለሥልጣን የከተማዋ ነዋሪዎች ማጨስ በተከለከለባቸው አካባቢዎች ትምባሆ ለማጨስ እሳት የሚጭሩ ሰዎችን ሲያገኙ አተኩረው እንዲመለከቷቸው አሳሰቡ።
ፕሮፌሰር ሎ ቹንግ ማው ይህን ያሉት ከትንባሆ ነጻ የሆነ ከተማ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ጊዜ ሲሆን፣ ፖሊስ እያንዳንዱን አጫሽ ይይዛል ተብሎ እንደማይጠበቅም ተናግረዋል።
ሆንግ ኮንግ አሁን ላይ የፀረ ትምባሆ ሕጓን ለማጥበቅ እየመከረች ነው።
በሆንግ ኮንግ ማጨስን ለመቀነስ የሕዝብ ውይይት ከተጀመረ በኋላ ፕሮፌሰር ሎ፣በአንድ የጤና ጉዳዮችን የተመለከተ ስብሰባ ላይ ለሕግ አውጪዎች ሕዝቡ ማጨስን ለመከላከል ሚና እንዳለው ገልጸው፣ ፖሊስ ግን በወቅቱ ደርሶ አጫሾች ላይ እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ተናግረዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ በምግብ ቤቶች፣ በሥራ ቦታዎች፣ በቤት ውስጥ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች እና በአንዳንድ የአደባባይ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ማጨስ ክልክል ነው።
የሕክምና ዶክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሎ "ማጨስ ለማንኛውም ሰው ጤና ጎጂ ነው፤ በመሆኑም ሆንግ ኮንግ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሕግ የማክበርና የማስከበር ባህል እንዲፈጠር ትፈልጋለች" ብለዋል።
ፕሮፌሰር ሎ ጨምረውም የከተማዋ ነዋሪዎች ማጨስ በተከለከለባቸው ቦታዎች የሚያጨሱ ሰዎችን ሲመለከቱ ሕግ አስፈጻሚ አካላት በአካባቢው ባይኖሩ እንኳን አጫሾችን አተኩረው በመመልከት ማሳቀቅ ይችላሉ ብለዋል።
ሎ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ሕግ እንደሚሻሻልም ገልጸዋል።
አሁን ላይ በከተማዋ የተቀመጠውን ሕግ መጣስ እስከ 192 ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ያስቀጣል።
ይሁን እንጅ በአካባቢው ፖሊስ ሲደርስ ወንጀሉ ቀድሞውኑ ቆሞ ሊሆን ስለሚችል እርምጃ መውሰድ አይችሉም።
በመሆኑም "የማጨስ ሕጎች ልክ አውቶብስ ለመጠበቅ እንደሚደረጉ ሰልፎች መተግበር ይገባል" ብለዋል ሎ።
“መቼም የአውቶብስ ሰልፍ ሕግ ያስፈልገዋል የሚል አይኖርም ።ማኅበረሰባችን አውቶብስ ለመጠበቅ ወረፋ ይዞ በመሰለፍ ሕግ የሚያከብርበትን ባህል መፍጠር ችሏል።በመሆኑም ሁሉም ማኅበረሰብ ያለማጨስ ባህልን መፍጠር እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
የሆንግ ኮንግ መንግሥት ከግምት ካስገባቸው ፀረ ትምባሆ አዳዲስ ሕጎች መካከል፣ ከሆኑ ዓመታት በኋላ የተወለዱ ሰዎች የትምባሆ ምርቶችን እንዳይገዙ መከለከል እና በሲጋራ ላይ የሚጣለውን ቀረጥ በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ይገኙበታል።