በኮፐንሃገን አንድ ግለሰብ በገበያ ማዕከል ውስጥ ተኩስ በመክፈት ሦስት ሰዎችን ገደለ

ታትሟል

የዴንማርክ መዲና ኮፐንሃገን በሚገኝ አንድ የገበያ ማዕከል ውስጥ ግለሰቡ በከፈተው ተኩስ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ብዙዎች መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ከቁስለኞቹ መካከልም ሦስቱ ክፉኛ የተጎዱ ናቸው ተብሏል።

በኮፐንሃገን ደቡባዊ ክፍል በሚገኘው ፊልድ የገበያ ማዕከል ውስጥ ይህንን ጥቃት የፈጸመው የ22 ዓመቱ ወጣት በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑ ታውቋል።

ፖሊስ ጥቃት ፈጻሚውን ያነሳሳው ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም ብሏል።

የዴንማርክ ጠቅላይ ሚንስትር ሜቴ ፍሬደሪክሰን “ዴንማርክ በጭካኔያዊ ጥቃት ተጎድታለች” በማለት ተጎጅዎችን በማጽናናት በእንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ወቅት አንድ ላይ እንዲቆሙ ዴንማርካዊያንን ጠይቀዋል።

 “ውቧ እና በሰላሟ የምትታወቀው መዲናችን በሽርፍራፊ ሴኮንዶች ተመሰቃቅላለች” ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሯ።

የዴንማርክ ዘውዳዊ ቤተሰብም የመጽናናት መልዕክቱን አስተላልፏል።

“ለደረሰው አስከፊ ነገር ምክንያቱን ባናውቅም ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውና መቁሰላቸው ግን ግልጽ ሆኗል” ብሏል ከንጉሳዊው ቤተሰብ የጣው መግለጫ።

 ጥቃቱን በመፈጸም የተጠረጠረው ወጣት፣ ጠመንጃ እና ተተኳሾችን እንደያዘ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪው ዛሬ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ፖሊስ ገልጿል።

ከጥቃቱ ጀርባ ሌሎች አቀናባሪዎች ስለመኖራቸው የተባለ ነገር ባይኖርም፣ የገበያ ማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ሱቆች ሁሉ ያሏቸውን የቪዲዮ ምስሎች ለማስረጃነት እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል።

ፊልድ የገበያ ማዕከል ከ140 በላይ ሱቆች እና ሬስቶራንት ያሉት ሲሆን ከመዲናዋ መውጫ አካባቢ የሚገኝ ነው።

 የዐይን ምስክሮች እንደሚሉት የጥይት ተኩሱን ተከትሎ ገበያተኞች ከፍተኛ ግርግርና መደናገጥ ተፈጥሮባቸው ነበር።

ኢዛቤል የተባለች የዓይን ምስክር ለዳኒሽ ሚዲያ በሰጠችው ምስክርነት “በድንገት የጥይት ድምጽ ሰማን። ይመስለኛል 10 አካባቢ ተኩስ ሰማን። ከእዚያ ሮጠን መጸዳጃ ቤት ውስጥ ገባን። በዚያች ትንሽ መጸዳጃ ቤት ውስጥ 11 ሰዎች ተፋፍገን ተደበቅን። በጣም ሞቃታማና አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ነበርን። በጣም አስደንጋጭ ጊዜ ነበር” ብላለች።

 ጥቃት ከተፈጸመበት የገበያ ማዕከል በተወሰነ ርቀት ላይ እንግሊዛዊው ሙዚቀኛ ሃሪ ስታይልስ ከደቂቃዎች በኋላ የሙዚቃ ኮንሰርት ሊያካሂድ ነበር። ሆኖም በተፈጠረው ችግር ምክንያት ኮንሰርቱ ተሰርዟል።

ኮንሰርቱ ከተሰረዘ በኋላ “እኔ እና ቡድኔ በኮፐንሃግን የገበያ ማዕከል ውስጥ ችግር ለደረሰባቸው ሁሉ እንጸልያለን። በጣም ደንግጫለሁ። እወዳችኋለሁ” በማለት ስናፕቻት ላይ መልዕክት አስተላልፏል።

 ከጥቃቱ በኋላ ንጉሳዊያን ቤተሰቦች ይዘዋቸው የነበሩ ፕሮግራሞች ተሰርዘዋል። ብዙ የጎረቤት አገራት መሪዎችም ሃዘናቸውን ገልጸዋል። የፊንላንድ፣ የአየርላንድ እና የኖርዌ መሪዎች በዴንማርክ በደረሰው ጥቃት ሃዘናቸውን ከገለጹት መካከል ናቸው።

 ዴንማርክ እንደእዚህ አይነት ጥቃት ያስተናገደችው ከሰባት ዓመት በፊት በፈረንጆቹ 2015 ሲሆን፣ በጥቃቱም ሁለት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 6 ፖሊሶች ደግሞ ቆስለው ነበር። በወቅቱም ጥቃት አድራሹ በፖሊስ ተገድሏል።