በኢራን ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በሚታሰሩበት ትልቁ እስር ቤት እሳት ተቀሰቀሰ  

በእስር ቤት የተነሳው እሳት

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/VAHID ONLINE

ታትሟል

የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞች እና የውጭ ሀገር ዜጎች በሚታሰሩበት ታዋቂው የኢራን ኢቪን እስር ቤት ቅዳሜ ዕለት ከፍተኛ እሳት ተቀስቅሷል።

በማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች እንዳሳዩት ቴህራን ከሚገኘው እስር ቤት የእሳት ነበልባል እና ጭስ ታይቷል። የተኩስ እና የፍንዳታ ድምፅም ተሰምቷል። 

ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሃሳባቸውን ያካፈሉ አንድ ባለስልጣን ሁኔታው ​​በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል። እሳቱ ከዚያ በኋላ መቀጠሉንም የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ታይተዋል።

ኢራን ለሳምንታት በፀረ-መንግሥት ተቃውሞ ተናውጣለች።

ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ባለፈው ወር የ22 ዓመቷ ኩርዳዊ ኢራናዊት ማህሳ አሚኒ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ህይወቷ ካለፈ በኋላ ነው።

ባለሥልጣናቱ በልብ ሕመም እንደሞተች ቢናገሩም ቤተሰቦቿም ሆኖም ተቋማት በሥነ ምግባር ፖሊሶች ተደብድባለች ሲሉ ተከራክረዋል።

በእስር ቤቱ ያለው ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ተቃውሞዎች ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም ተብሏል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ወደ ኢቪን በመላካቸው ከተቃውሞው ጋር ሊያያዝ ይችላልም ብለዋል። 

የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ሁለቱ ግንኙነት እንደሌላቸው አሳውቀዋል።

 አንድ ባለስልጣን ለእሳቱ ተጠያቂ የሆኑት "ወንጀለኛ አካላት" ናቸው ብለዋል። ስምንት ሰዎች መቁሰላቸውንም በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኘው ኢአርኤን ዘግቧል።

ከእስር ቤቱ ውስጥ ሆነው ለመንግሥት ቴሌቭዥን የተናገሩት የቴህራን ገዥ በጥቃቅን ወንጀል የሚታሰሩ ሰዎች በሚኖሩበት የእስር ቤቱ ክንፍ ረብሻ እንደነበር እና አሁን ሁኔታው ​​ሙሉ በሙሉ መረጋጋቱን ጠቁመዋል።

ኢአርኤን ያጋራቸው ምስሎች ከእሳቱ በኋላ በእስር ቤቱ ውስጥ የደረሰውን ጉዳት ያሳያሉ ተብሏል።

የእሳቱ እና የጭሱ ምስሎች በማህበራዊ ድር አምባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቁት ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ነው።

የተኩስ እና ፍንዳታ ድምጾች በበርካታ ቪዲዮዎች ላይ ተሰምተዋል። ከእስር ቤቱ ውጭ ሰዎች “ሞት ለአምባገነኑ” ሲሉ ተሰምቷል። 

ይህ ከፀረ-መንግስት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ዋና መፈክሮች አንዱ ነው።

አንድ ቪዲዮ ከእስር ቤቱ ውጭ የተተኮሱ ነገሮችን ከሳየ በኋላ የፍንዳታ ድምጽ መከተሉን ቢቢሲ ፐርዢያ ዘግቧል።

ከማረሚያ ቤቱ ውጭ ብዙ ህዝብ ሲሰበሰብ፣ የትራፊክ መጨናነቅም ተፈጥሯል። የአድማ በታኝ ፖሊሶች ወደ ተቋሙ ሲገቡ ታይተዋል።

የኢራን መገናኛ ብዙሀን መረጋጋት እንደተፈጠረ ከተናገሩ በኋላም የእስር ቤቱ ሁኔታ ግራ አጋቢ እንደነበር ተነግሯል። 

 እሳቱ መቀጣጠሉ መቀጠሉን እና የተኩስ ድምጽ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ መታየታቸውን ቀጥለዋል።

በእስር ቤት የተነሳው እሳት

የፎቶው ባለመብት, TWITTER

ሌሎች ደግሞ የፖለቲካ እስረኞች እና ባለፉት አራት ሳምንታት ውስጥ የታሰሩ በርካታ ተቃዋሚዎች በሚገኙበት የእስር ቤቱ ጣሪያ ላይ ታይተዋል ተብሏል። 

የአንዳንድ እስረኞች ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዘመዶቻቸውን በስልክ ማግኘት አልቻሉም። ቀደም ሲል ስልክ ይሠራ የነበረ ሲሆን በእስር ቤቱ አካባቢ ያለው የኢንተርኔት ግንኙነትም የተቋረጠ ይመስላል።

እንግሊዝ ኢራናዊ የሆኑት ናዛኒን ዛጋሪ-ራትክሊፍ እና አኖሼህ አሹሪ ከስለላ ጋር በተያያዘ ለብዙ ዓመታት በኢቪን ታስረው ነበር። እነሱ ክሱን ሲያስተባብሉ ቆይተው በኋላ ላይ ተለቀዋል።  

እስር ቤቱ በምዕራባውያን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲተች ቆይቷል። ሂዩማን ራይትስ ዎች በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ባለስልጣናትን የማሰቃየት፤ በረዥም ምርመራ እና ለታሳሪዎች የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ከልክለዋል ሲሉ ይከሳሉ።

ዜጎቻቸው በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ አንዳንድ ሃገራት ስጋታቸውን አሰምተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ሁኔታውን “በጥንቃቄ” እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል። የእንግሊዝ መንግስት የደህንነት ሚኒስትር በበኩላቸው “በጣም አሳሳቢ” ሲሉ ገልጸውታል።

አሚኒ ህይወቷ ካለፈ በኋላ ኢራን በተቃውሞዎች ስትናጥ ቆይታለች። ይህም ኢራን እአአ በ1979 ኢስላሚክ ሪፐብሊክ በመሆን ከተመሠረተች በኋላ ትልቁ ተቃውሞ መሆኑን ይነገራል። 

በተቃውሞው ህይወታቸው ካለፉት መካከል ብዙዎቹ ታዳጊዎች ናቸው።