ቀጣይ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ እኩለ ቀን ይለያል

ዩናይትድ ኪንግደምን ለመምራት እየተወዳደሩ ያሉት ሊዝ ትረስ እና ሪሺ ሱናክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ተሰናባቹን የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት በመወዳደር ላይ ከሚገኙት ሊዝ ትረስ ወይም ሪሺ ሱናክ መካከል አሸናፊው ዛሬ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ቀን ላይ ይታወቃል።

አሸናፊው ግለሰብ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለ ኢኮኖሚን እና በ40 ዓመታት ከፍተኛው የተባለለትን የዋጋ ግሽበት የሚረከብ ይሆናል።

ቀጣዩ መሪ የተከማቸ ኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያን መሰረዝን ጨምሮ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦችን ለመርዳት እቅድ መያዙን ቢቢሲ ከምንጮቹ ተርድቷል።

ይህን ምርጫ ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብሎ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ሊዝ ትረስ ኃላፊነቱን በተረከቡ በአንድ ሳምንት ግዜ በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ጫና ውስጥ የሚገኙ ሸማቾችን መደገፍ የሚያስችሉ እገዛዎችን ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

እንዲሁም በመስከረም ወር መጨረሻ ወደ 30 ቢሊዮን ፓውንድ ገደማ የግብር ቅነሳ ይፋ ለማድረግ ማሰባቸውንም ትረስ አስታውቀዋል።

ተቀናቃኛቸው ሱናክ ውድድሩን ተሸንፌአለሁ ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመው “አሁን ዋና ስራዬ ወግ አጥባቂው ፓርቲ የሚመራውን መንግሥት መደገፍ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ትረስ ከኃይል አቅርቦት ዋጋ ቅናሽ እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ከማቀዳቸው ባሻገር ዝርዝር የእርምጃ እቅዳቸውን እስካሁን ድረስ ይፋ አላደረጉም።

በአሁን ወቅት የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱን በመምራት ላይ የሚገኙት እጩዋ እሁድ በቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የእቅዳቸውን ዝርዝር ሁኔታ ይፋ ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ላይ ተቀምጠው ተጨማሪ ግዜ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

ዕቅዳቸው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች ብቻ ነው ወይስ ለሁሉም ዜጎች የሚለውን ሳይመልሱም ቀርተዋል።

ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታም ባለፉት 20 ዓመታት ለነበረው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት ተጠያቂው ፍትሃዊ የሃብት ስርጭትን ማስፈን በሚል ሲተገበር የቆየው የግብር ፖሊሲ ነው ብለዋል።

የሠራተኛ ፓርቲ፣ ሊበራል ዴሞክራቶች እና ኤስኤንፒ መንግሥት ቢሊዮን ፓውንዶችን አውጥቶ የኃይል ዋጋ ድጎማ እንዲያደርግ የጠየቁ ሲሆን የግሪን ፓርቲ አባላት ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አምስት ግዙፍ የኃይል አቅራቢ ተቋማትን ባለቤትነቱን ከግለሰቦች እንዲረከብ ጠይቀዋል።

የመሪነቱን ቦታ ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁት ትረስ የተከማቸ የኃይል ክፍያን መሰረዝን ውድቅ ባያደርጉም ከዚህ ቀደም ባደረጉት ክርክር አገራቸው እንግሊዝ የአገር ውስጥ የኃይል አቅርቦት ምንጮቿን ማሳደግ ግድ እንደሚላት ትኩረት ሰጥተው ነበር።

ለሰባት ሳምታት የዘለቀው የዩኬ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ለመያዝ የተደረገው ፉክክር የቦሪስ ጆንሰንን የሶስት ዓመት የስልጣን ዘመን ቆይታ ማብቂያ የሚያሰምር ይሆናል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ቦሪስ ጆንሰን ከፓርቲያቸው መሪነት ለመልቀቅ የወሰኑት ሪሺ ሱናክን ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮቻቸው አመራራቸውን በመቃወም በ48 ሰዓታት ውስጥ በፈቃዳቸው ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ነው።

በመጀመሪያው ዙር 11 ተወዳዳሪዎች የወግ አጥባቂውን ፓርቲ ለመምራት አቅደው ወደ ውድድር ግብተው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ሁለት ዝቅ ብሏል።

ምንም እንኳን የሕንድ የዘር ግንድ ያላቸው ሱናክ በፓርላማ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ቢኖራቸውም የውጪ ጉዳይ ኃላፊዋ ትረስት አሸናፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ትንበያዎች ያሳያሉ።

ተሰናባቹ ቦሪስ ጆንሰን የስልጣን ርክክብ ከመደረጉ በፊት ማክሰኞ የስንብት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን የሚያሸንፈው ተወዳዳሪ እስካሁን ባለው ባህል መሠረት በባኪንግሃም ፓላስ ሳይሆን ወደ ስኮትላንድ በመጓዝ በባልሞራል ቤተ-መንግሥት ሲመቱን ከንግስቲቱ የሚቀበል ይሆናል።

ለዚህም ምክንያቱ ንግስቲቱ በጤና ምክንያት እንደልባቸው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ባለፈው ሳምንት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ነው።