ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት ይፋዊ ያልሆነ ውድድር ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ ከካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውና ከምክር ቤት አባላት ድጋፍ ሳያገኙ በመቅረታቸው ከወግ አጥባቂው ፓርቲያቸው መሪነት መልቀቃቸውን ተከትሎ እርሳቸውን ለመተካት ፉክክር ተጀምሯል።
የፓርላማ አባሉ ቶም ቱጌንዳት ይህንን ውድድር ተቀላቅለው፣ የቦሪስን ቦታ ለመተካት ፍላጎት ያሳዩትን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሱዌላ ብሬቨርማን እና ስቴቭ ቤከርን ተቀላቅለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ፣ እርሳቸውን የሚተካ ሰው እስከሚገኝ እስከ መስከረም ድረስ በጠቅላይ ሚንስትርነት በሥልጣናቸው ላይ ለመቆየት አቅደዋል።
ሆኖም በርካታ ባልደረቦቻቸው እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አሁኑኑ ሥልጣን እንዲለቁ ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክፍት የነበሩትን የካቢኔ ቦታዎችን በሌሎች ተክተዋል።
በርካታ የካቢኔ አባላሎቻቸው አስተዳደራቸውን በመቃወም ሥራ ከለቀቁ በኋላ ቦሪስ ጆንሰን ሥልጣናቸውን ይዘው ለመቆየት ለሁለት ቀናት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ካደረጉ በኋላ ሐሙስ ዕለት ከፓርቲ መሪነት እንደሚነሱ ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በከፍተኛ እና በዝቅተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ የነበሩ ወደ 60 የሚጠጉ የወግ አጥባቂ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ከመንግሥት ኃፊነት መልቀቃቸው መንግሥት ኃላፊነቱን ለመወጣት ያለውን አቅም ጥራጣሬ ውስጥ ከቶታል።
ቦሪስ ጆንሰን አዲስ ለተሾሙት ካቢኔ አባሎቻቸው ሐሙስ ዕለት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ቀሪ ጊዜያቸውን ዋና ዋና የፖሊሲ ለውጦችን ለማድረግ እንደማይጠቀሙበት ቃል ገብተዋል።
የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አመራር ውድድር የጊዜ ሰሌዳ በሚቀጥለው ሳምንት የሚታወቅ ሲሆን፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ መስከረም ወር ማብቂያ ድረስ ይሾማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ውድድሩ በመካሄድ ላይ ነው።
የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቱገንዳት፣ አርብ ዕለት ለዴይሊ ቴሌግራፍ በጻፉት ጽሁፍ የአመራርነት ወድድራቸውን የጀመሩ ሲሆን “የግብር ቅነሳ እና አዲስ ጉልበትና ሃሳብ” ይዘው እንደሚመጡ ቃል ገብተዋል።
የቦሪስ ጆንሰን ቀንደኛ ተቺ የነበሩት የቀድሞ ወታደር ቱገንዳት “ከዚህ ቀደም በጦሩ ውስጥ አገልግያለሁ፣ አሁን ደግሞ በፓርላማ ውስጥ እየሰራሁ ነው። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የቀረበልኝን ጥሪ ለመመለስ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ብራቨርማን በበኩላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚወዳደሩ አረጋግጠዋል።
የብሬግዚት ሚኒስትሩ ቤከርም ሰዎች ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲወዳደሩ ከጠየቋቸው በኋላ ለመወዳደር እንዳሰቡ ተናግረዋል።
የቦሪስ ጆንሰን ተቃዋሚ የነበሩት የቀድሞው የጤና ኃላፊ ሳጂድ ጃቪድ እና የትራንስፖርት ኃላፊ ግራንት ሻፕስም ውድድሩን ለመቀላቀል እንዳሰቡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሊዝ ትረስ፣ የቀድሞ ቻንስለር ሪሺ ሱናክ እና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጀረሚ ሃንትም በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይገመታል።
በሚቀጥሉት ቀናት በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ገለጻ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ሆኖም ማይክል ጎቭ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ እና የቀድሞ የጤና ኃላፊ ማት ሃንኩክን ጨምሮ የቀድሞ የፓርቲው አመራር አባላት እንደማይወዳደሩ ተናግረዋል።












