ሃላንድ ወደ ማድሪድ ይሄድ ይሆን? ውሉ እያበቃ ያለው ራሽፈርድ ዕጣ ፈንታስ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሪያል ማድሪድ ‘ኦፕሬሽን ሃላንድ’ የተሰኘውን ዘመቻ እንደ አዲስ ቀስቀሶታል።
የስፔኑ ክለብ የ22 ዓመቱን ኖርዌጂያን አጥቂ ከማንቸስተር ሲቲ ለማስፈረም የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም ብሏል።
ማድሪድ፤ ሃላንድን ከእንግሊዝ ወደ ስፔን ማምጣት የፈለገው በፈረንጆቹ 2024 ሲሆን፣ ዋጋው 240 ሚሊዮን ዩሮ ሊደርስ ይችላል ሲል ኤኤስ የተሰኘው የስፔን ጋዜጣ ዘግቧል።
በሌላ የአውሮፓ እግር ኳስ ዜና ባየር ሙኒክ የ35 ዓመቱ አሠልጣኝ ጁሊያን ናግልስማንን አሰናብቷል።
በምትኩ ጀርመናዊው የቀድሞ የፒኤስጂ እና የቼልሲ አሠልጣኝ የነበረውን ቶማስ ቱኽል ለማምጣት ወስኗል ያለው የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ ነው።
የእንግሊዝ እና የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ ማርከስ ራሽፈርድ ከክለቡ ጋር ያለውን ውል እንደማያራዝም 90ሚን ድረ-ገፅ ጽፏል።
ራሽፈርድ ውሉን ለማራዘም ያመነታው ክለቡ ሊሸጥ በመቅረቡ አዲሱ የማንቸስተር ባለቤት ማን ሊሆን ይችላል የሚለው እስኪወሰን ነው ብሏል ገፁ።
ከአሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ያለው ቶተንሃም ፊቱን ወደ ናግልስማን ሊያዞር እንደሚችል ፉትቦል ለንደን ጽፏል።
ቼልሲ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ኒውካስል ዩናይትድ የ19 ዓመቱን የጁቬንቱስ የክንፍ መስመር ተጫዋች ሳሙዔል ኢሊንግን ለማስፈረም እየተሽቀዳደሙ ነው።
አርሰናል ደግሞ የባርሴሎናውን ታዳጊ አሊያስ አኮማችን ለማስፈረም ከኤሲ ሚላን እና ሲቪያ ጋር መፎካከር ጀምሯል።
ሊቨርፑል እና ታሪካዊ ተቀናቃኛቸው ማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾችን አድኖ በማቅረብ አቻ አይገኝለትም የሚባለውን መልማይ ለማስፈረም ተናንቀዋል።
እንደሚረር ዘገባ ከሆነ የ41 ዓመቱ ተጫዋች መልማይ ፖል ሚሼል በሚቀጥለው ክረምት ሞናኮን ይሰናበታል።
ኃያላኑ ማንቸስተር ሲቲ እና ፒኤስጂ የ16 ዓመቱን ክሮኤሺያዊ ታዳጊ ሉካ ቩስኮቪች የግል ንብረታቸው ለማድረግ እየተፎካከሩ ነው የሚለው ፋብሪዚዮ ሮማኖ ነው።
ለፓልሜይራስ የሚጫወተው የ19 ዓመቱን ብራዚላዊ አጥቂ ጂዮቫኒን ለማስፈረም ከኒውካስል ጋር እየተፎካከረ የሚገኘው ኤቨርተን፣ ፈረንሳዊውን አጥቂ ኒል ሞፔ በሚቀጥለው ክረምት እንሚሸጥ ፉትቦል ኢንሳይደር ዘግቧል።
አርጀንቲናዊው የፒኤስጂ አጥቂ ወደ ባርሴሎና የመመለሱ ነገር አይቀሬ ነው ሲል፣ የዘገበው ደግሞ 90ሚን ነው።
የ35 ዓመቱ ሜሲ በፒኤስጂ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ቢሆንም፣ ክለቡ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውጭ መሆኑ የተጫዋቹን ዕጣ ፈንታ ወስብስብ አድርጎታል።
በሌላ ዘገባ ባርሴሎና ለቀድሞው የስፔን እግር ኳስ ዳኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ክፍያ ፈፅሟል የሚል ክስ መቅረቡን ተከትሎ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ቅጣት ይጠብቀዋል በማለት ሰን ጋዜጣ አስነብቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ጉዳዩን የሚመረምር ኮሚቲ ያቋቋመ ሲሆን፣ ባርሴሎና በሚቀጥለው ዓመት ከአውሮፓ ውድድሮች ሊታገድም ይችላል።
ሚረር የተሰኘው የእንግሊዝ አውድ የማንቸስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ቪክተር ሊንዴሎፍ ከክለቡ ጋር ይቆይ አይቆይ በሚቀጥለው ክረምት ይለያል ብሏል።
የመገናኛ ብዙኃን ትኩረትን የሳበው የማንቸስተር ዩናይትድ ሽያጭ ጉዳይ አሁን አነጋጋሪነቱን ቀጥሏል።
ክለቡ ለሽያጭ ከቀረበ ወዲህ የተለያዩ ባለሃብቶች ማንቸስተር ዩናይትድን በረብጣ ፓውንድ ለመግዛት ቢጫረቱም የግሌዘር ቤተሰብ ሙሉ በሙሉ መሸጥ ላይፈልጉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።












