ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ንግሥት ኤልዛቤት የተደገሰላቸው የ70ኛ ዓመት ክብረ በዓል እንዳስደሰታቸው ገለጹ
የዩናትድ ኪንግደም እና የሌሎች በርካታ አገራት ንግሥት የሆኑት ዳግማዊት ኤልዛቤት የ70ኛ የንግሥና ክብረ በዓላቸውን ለማክበር በተከናወነው ሥነ-ሥርዓት መደሰታቸውን ገለጹ።
ከሐሙስ ግንቦት 25 እስከ ግንቦት 28/2014 ለአራት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው የንግሥና በዓል መጠናቀቁን ተከትሎ የምስጋና ደብዳቤ ጽፈዋል።
ንግሥት ኤልዛቤጥ በምስጋና ደብዳቤያቸው ከቤተሰብ አባላት በሚያገኙት ድጋፍ ሕዝቡን ለማገልገል አሁንም ቁርጠኛ ነኝ ብለዋል።
የንግሥና በዓሉን ለመዘከር በሁሉም ሥነ-ሥርዓቶች ላይ መገኘት ያልቻሉት ንገሥቲቱ፤ “በልቤ ግን ሁሌም ከእናንተ ጋር ነበርኩ” ብለዋል።
የሥነ-ሥርዓቱ ማጠናቀቂያ ላይ ከንጉሣውያን ቤተሰብ ጋር ሆነው ከባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ሰገነት ላይ ቀርበው ለታዳሚው ሰላምታ አቅረበዋል።
በመላው ዩናትድ ኪንግደም የተዘጋጁትን ሥነ-ሥርዓቶች እና የሙዚቃ ድግሶችን በሺዎቹ የሚቆጠሩ በአካል በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮት ተከታትለዋቸዋል።
የ96 ዓመቷ አዛውንት ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት የንግሥና ክብረ በዓላቸውን ለማክበር አደባባይ በተገኙ ሰዎች ቁጥር መደነቃቸውን ጽፈዋል።
ንግሥት ኤልዛቤት ከዩናትድ ኪንግደም በተጨማሪ የካናዳ፣ የአውስትራሊያ፣ የኒው ዚላንድ፣ የጀማይካ እና የሌሎች 10 አገራት ንግሥት ናቸው።
ንግሥቲቱ ለሰባት አስርት ዓመታት በዘውዳቸው ላይ የቆዩበትን ጊዜ ለማክበር ለአራት ቀናት በተካሄደው ሥነ ሥርዓት የተለያዩ ዝግጅቶችተካሂደዋል።
ከእነዚህም መካከል ወታደራዊ ሰልፍ ትርኢት፣ በቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል ልዩ ጸሎት ሥነ ሥርዓት እና በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ውስጥ የሙዚቃ ድግስ ከተካሄዱት ዝግጅቶች መካከል ዋናዎቹ ናቸው።
ለቀናት የቆየው የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ትናንት እሁድ በለንደንና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ በተካሄዱ የተለያዩ ዝግጅቶች ተጠናቋል።