ሕንዳዊቷን በደቦ ደፍረው በመግደል ሞት የተፈረደባቸው ግለሰቦች መፈታት የፈጠረው ድንጋጤ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአስር ዓመት በፊት በሕንድ በርካቶችን ያስደነገጠ እና ያስቆጣ ሁኔታ ተፈጠረ።
አንዲት የ19 ዓመት የዴልሂ ሴት በአጎራባቿ ሃሪያና ግዛት በሚገኝ ሜዳ ላይ በቡድን ተደፍራ ተገደለች።
በሕንድ ሕግ መሠረት ትክክለኛ ስሟ እንዲገለጽ ያልተደረገው እና ‘አናሚካ’ ተብላ የተጠራች ሴት ላይ የተፈጸመ የጭካኔ ግድያ ይፋ ሆነ።
የሕንድ መገናኛ ብዙኃን የጭካኔውን ዝርዝር ይዘው መውጣታቸውን ተከትሎ በርካቶች ተቆጡ።
በድርጊቱም ሦስት ወንዶች ጥፋተኛ ሆነው ተገኙ። በአውሮፓውያኑ 2014 የሞት ቅጣት ተፈረደባቸው።
ከጥቂት ወራት በኋላም የዴልሂ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣቱን በማረጋገጥ ብያኔውን አጸና።
ነገር ግን ሰኞ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም. የሕንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በርካቶችን ባስደነገጠ መልኩ ግለሰቦቹን በነጻ አሰናበተ።
ለዚህም ግለሰቦቹ ወንጀሉን መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ ምንም “የሚያሳምን፣ የተጣራ እና ግልጽ ማስረጃ” የለም በማለት ነፃ አውጥቷቸዋል።
ሦስቱ ዳኞች ውሳኔውን ባስተላለፉበት ችሎት ላይ በፖሊስ ምርመራ ላይ ከበድ ያሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፣ ፍርድ ቤቱ የነበረበትንም ጉድለት በመገምገም ዳኛው ትክክለኛ ውሳኔ አልወሰኑም ብለዋል።
ውሳኔው የተበዳይዋን ወላጆች ያስቆጣ፣ የመብት ተሟጋቾችን እና የሕግ ባለሙያዎችን አስደንግጧል።
በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመደፈር ወንጀሎች በሚፈጸምባት አገር በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ቁጣን አስከትሏል።
“በሕንድ በ2022 ፍትህ እንደዚህ ይመስላል” ሲል አንድ የትዊተር ተጠቃሚ የሟችን አባት ፎቶ በማጋራት ቁጣውን አስፍሯል።
አንዳንዶች የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በቅርቡ የጉጃራት ግዛት ካደረገው ጋር አነጻጽረውታል።
በግዛቷ በአውሮፓውያኑ 2002 ከነበረው የሃይማኖት ብጥብጥ ጋር ተያይዞ ቢልኪስ ባኖ የተባለችው ነፍሰ ጡር ሙስሊም ሴት በቡድን በመድፈር እና ዘመዶቿን በመግደል የተከሰሱት ግለሰቦች የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩ ግለሰቦች በቅርቡ በነፃ ወጥተዋል።
“ፍትህ የማግኘት ተስፋዬ በደቂቃዎች ውስጥ ጨለማ ውስጥ ገባ” ሲሉም የአናሚካ አባት ተናግረዋል።
“ለፍትህ ለማግኘት ለ10 ዓመታት ጠብቀን ነበር። በፍትህ አካላት ላይ እምነት ነበረን፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሞት ፍርዱን እንደሚያጸናና እና የልጄ ገዳዮች በመጨረሻ እንደሚሰቀሉ አምነን ነበር” ብለዋል።
የ19 ዓመቷ ሴት በደቡብ-ምዕራብ ዴልሂ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ነዋሪዎች በሰፈሩበት ገጠራማ አካባቢ ቻውላ ነዋሪ ነበረች።
ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በመዲናዋ ዴልሂ ዳርቻ በጉራጎን በሚገኝ የጥሪ ማዕከል ውስጥ ሥራ ጀመረች። በዚህም ደመወዝ ቤተሰቧን በብቸኝነት የምታስተዳድረው እሷ ሆነች።
“የመጀመሪያ ደሞዟን ተቀብላ በደስታ ላይ ነበረች” በማለት ላለፉት ስምንት ዓመታት ቤተሰቡ ፍትህ ለማግኘት በሚያደርገው ትግል ስትረዳ የቆየችው የመብት ተሟጋች ዮጊታ ብሃይና ተናግራለች።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 9/2012 አመሻሽ ላይ አናሚካ ከሦስት ጓደኞቿ ጋር ከሥራ ወደ ቤት እየተመለሰች ሳለ ታገተች።
ወንዶቹ ቀይ መኪና እያሽከረከሩ ነበር።
ከአራት ቀናት በኋላ አስከሬኗ ተቆራርጦ የተወሰነውም የሰውነት ክፍሏ ታቀጥሎ ተገኘ።
ከዓመታት በፊት በነበረው የፍርድ ሂደት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የተገኘው ማስረጃ ምንም ክፍተት የሌለው ነው በማለት ተከራክሯል።
ካቀረባቸው ማስረጃዎች መካከል፡
- ከሦስቱ ተከሳሾች የአንዱ የኪስ ቦርሳ ወንጀሉ በተፈጸመበት ስፍረሰ በመገኘቱ ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን መፈጸማቸው መናዘዛቸው፤
- የተጎጂዋ ልብስም የት እንደነበር እና አስከሬኗም የት እንዳለ ለፖሊስ መምራታቸው፤
- በመኪናው ውስጥ የተገኘው ደም፣ የወንድ ዘር ፈሳሽ እንዲሁም የፀጉር ዘረ መል (ዲኤንኤ) ናሙናዎች ተከሳሾቹ እና ሟቿ በተሽከርካሪው ውስጥ እንደነበሩ ማረጋገጫ መሆኑ ለፍርድ ቤት ቀርቧል።
ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤት በግለሰቦቹ ላይ የጥፋተኝነት ብይን በመስጠት ከሁለት ዓመት በኋላ የሞት ቅጣት በይኖባቸዋል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤትም የሞት ፍርድ ቅጣቱን አጸና።
ነገር ግን ሰኞ በቀረበው በባለ 40 ገፅ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሁኔታው ሌላ መልክ ያዘ።
በዳኛ ቤላ ትሪቪዲ አዘጋጅነት በወጣው ትዕዛዝ መሰረት ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ጥርጣሬ የሚፈጥሩና ምናልባትም ጣልቃ ገብነት የታየባቸው ነበሩ ብሏል።
ፍርድ ቤቱ “በፖሊስ በቀረቡ ማስረጃዎች እና በምስክሮች ቃል ውስጥ ያሉ አለመግባባቶች እና ቅራኔዎች” አሉ ብሏል።
ፍርድ ቤቱ በአዲሱ ትዕዛዝ ያቀረበውም፡
- ተከሳሾቹ በሟቿ ጓደኞች ወይም አጋቾቿን ለመታገል በሞከረው ወንድ ምስክር አልተለዩም።
- የዴልሂ ፖሊስ አገኘሁት ያለው የተከሳሹ ሰነዶችን የያዘው የኪስ ቦርሳ (ዋሌት)፣ ወይም የመኪና መካላከያ ቁርጥራጭ በወንጀሉ ቦታ በተነሳው የመጀመሪያው ፎቶ ላይ አልታየም ብሏል።
- መጀመሪያው በስፍራው የደረሱት የሃሪያና ፖሊሶች በሪፖርታቸው ውስጥ እነዚህን ነገሮች አልጠቀሰም።
- እነዚህ ቁሶች ምርመራውን ይመራ በነበረው ባለሥልጣን የዕቃዎች ዝርዝር ማስታወሻ ውስጥ አልተጠቀሱም።
- ፖሊስ አገኘሁት ያለው የታዳጊዋ ስልክ የእሷ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ አባቷ አላዩትም።
- ፖሊስ ወንጀሉ ተፈጽሞበታል በሚል የያዘው ቀይ መኪና ወንጀሉ ከተፈፀመበት ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ ሙሉ በሙሉ አልተረጋገጠም።
- ተከሳሾቹ የታሰሩበት ሁኔታ አጠያያቂ ነበር።
- አንዳንድ ተከሳሾች አለመመርመራቸው ጥርጣሬውን የበለጠ አጉልቶታል።
ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም ከመኪናው የተወሰዱት ማስረጃዎች ለፎረንሲክ ምርመራ የተላኩት በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነው።
“በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ናሙናዎች የመነካካት እና የመለወጥ ዕድል የመኖሩን ሁኔታ ማስወገድ አይቻልም” ሲሉ ጽፈዋል።
“በአስከፊ ወንጀል ተከሰው አለመቀጣት በአጠቃላይ በሕብረተሰቡ እና በተለይም በተጎጂ ቤተሰቦች ላይ ቁጣንም ሆነ ህመምን ሊፈጥር ይችላል” በማለት ፍርድ ቤቱ “ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን ማቅረብ አልቻለም” ብሏል።
ዐቃቤ ሕግ ክሱን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማምጣት አልቻለም፤ ምንም እንኳን የተከሰሱት በጣም በአስከፊ ወንጀል ቢሆንም ተከሳሾቹን በነፃ ከመልቀቅ ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም ብለዋል።
ቢቢሲ በዚህ ላይ አስተያየት እንዲሰጡት ለአንድ ከፍተኛ የዴልሂ ፖሊስ ባለሥልጣናት በኢሜይል ልኳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአናሚካ ቤተሰብ ጠበቃ ቻሩ ዋሊ ካናና ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ትዕዛዝ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ ይግባኝ እንደሚጠየቅበት እና የአቤቱታም ፊርማ እንደሚገባ ተናግረዋል።
“ይህ ፍርድ በጣም ግልጽ ያልሆነ እና ከፍተኛ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚያነሳ ነው። የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንደሚለው ማስረጃዎቹ ጣልቃ ገብነት ታይቶባቸው ሊሆን ይችላል ይላል። ነገር ግን ፖሊስን ላይ ክስ አያቀርብም” ብለዋል።
“ትዕዛዙ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃ እንደሌለ ቢገልጽም በተከሳሾቹ ላይ የቀረቡ በርካታ ማስረጃዎችን ችላ ብሏል” ሲሉም አስረድተዋል።
በአንድ ትምህርት ቤት በጥበቃነት የሚሠሩት የአናሚካ አባት፣ ሰኞ ዕለት ከሌሊት የሥራ ፈረቃቸው በኋላ በቀጥታ ወደ ፍርድ ቤት እንዳመሩ ተናግረዋል።
ውሳኔው ሲነበብ ከአናሚካ ወላጆች ጋር ከፍርድ ቤት ውጪ የጠበቀችው የመብት ተሟጋቿ ባሃይና በብይኑ ከፍተኛ ቁጣ እና ብስጭት እንደተሰማት ተናግራለች።
“ልቤ ተሰብሯል፣ የተሰማኝን ስሜት ለማስረዳት ቃል የለኝም። እኔ እንደዚህ ከሆንኩ ወላጆቸቿ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል” በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በምርመራው ላይ ስጋት ቢኖረው ኖሮ ጉዳዩን እንደገና መክፈት፣ ሌላ ምርመራ ማዘዝ ወይም ጉዳዩን ለፌደራል ፖሊስ ማስረከብ ይችል እንደነበር ትናገራለች።
“እውነታው አንዲት ወጣት በቡድን ተደፍራ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላለች፤ ፍርድ ቤቱ ለቤተሰቧ አንድ ዓይነት መፍትሄ መስጠት አለበት” ትላለች።
የአናሚካ አባት ግን ግራ በተጋባ ስሜት ላይ ናቸው።
“ከሰማይ መብረቅ የወረደብኝ እና የተመታሁ ነው የመሰለኝ” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምንድን ነው ያደረገው? ፍርድ ቤቶች ለ10 ዓመታት ያህል ምንም ጥርጣሬ አልነበራቸውም። ታዲያ ሁሉም ነገር እንዴት በድንገት ሐሰት ሊሆን ቻለ?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
“ሁሉም ሰው ሕንድ ለሴቶች እና ለታዳጊዎች ደኅንነቷ የተጠበቀ አይደለም ይላል። ከዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ በሕንድ ውስጥ ያለች የትኛዋም ታዳጊ ደኅንነት አይሰማትም። ወንጀለኞችን የበለጠ ያበረታታል” ሲሉ በሐዘን በተሰበረ ሁኔታ ተናግረዋል።












