በኢትዮጵያ ቀንሶ የነበረው የኮቪድ-19 ሕሙማን ቁጥር ባለፉት ቀናት መጨመሩ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI
በኢትዮጵያ ቀንሶ የነበረው የኮቪድ-19 ሕሙማን ቁጥር ከቅርብ ቀናት ወዲህ እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ለወረርሽኙ የስርጭት መጠን መጨመር ምክንያት ከሆኑ መካከል የማኅበረሰቡ መዘናጋትና ክትባት አለመውሰድ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።
በአዲስ አበባ የኮቪድ-19 ሕሙማንን ተቀብለው ሕክምና ከሚሰጡ ሆስፒታሎች ቀዳሚ የሆነው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ አግደው፤ ካለፉት 10 ቀናት ወዲህ በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን እና የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱን ባጋጠሟት አራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕበሎች ውስጥ ሕሙማንን ሲቀበል የነበረው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል፣ ወረርሽኙ ተከስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ መጋቢት 27 ቀን 2041 ዓ.ም. ያለ ታካሚ ማደሩን ማስታወቁ ይታወሳል።
ነገር ግን ካለፉት ቀናት ወዲህ ሁኔታው ተቀይሮ በወረርሽኙ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ እንደመጣ ዶ/ር ያሬድ ገልጸዋል።
“አንድ ሁለት እያለ ሕመምተኛ መምጣት ጀመረ። ባለፉት 10 ቀናት ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታካሚ ወደ ሆስፒታላችን እየገባ ነው። በቀን 10 እና 13 ሰዎችም ወደ ሆስፒታል ገብተው ሕክምና እየጀመሩ ይገኛሉ” ብለዋል።
አሁን ላይ ወደ 80 ታካሚዎች በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እንደሚገኙ እና ከእነዚህ ታካሚዎች ሦስቱ በጽኑ ሕሙማን ክፍል እንደሚገኙ ዶ/ር ያሬድ ተናግረዋል።
“ወረርሽኙ በአዲስ መልክ እየተፋፋመ እንደሆነ የሚያሳይ ቁጥር ነው በእኛ ሆስፒታል ያለው” ሲሉም አክለዋል።
ወረርሽኙ በዕድሜ የገፉና ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚበረታ ቢሆንም፣ በአሁን ወቅት በሆስፒታሉ ውስጥ ሕክምና እያገኙ ያሉት ከሕፃናት ጀምሮ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አዛውንቶች እንዲሁም ነፍሰ ጡር እናቶችም ጭምር እንደሆኑ አክለዋል።
አያይዘውም ተጓዳኝ ሕመም የሌለባቸው ወጣቶችም በወረርሽኙ እየተያዙ እንደሆነ ጠቅሰው “መዘናጋት አያስፈልግም” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ከሚያዝያ 2014 ዓ.ም. መባቻ ወዲህ ለተከታታይ 40 ቀናት በሆስፒታላቸው ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዘ ሞት አልተመዘገበም ነበር።
ባለፉት አምስት ግን በሆስፒታላቸው የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል።
ሆስፒታሉ መጋቢት 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበሩ የሕክምና ባለሙያን አክሞ ከሸኘ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ታካሚ ማደሩ ይታወሳል።
ከዚያ በኋላ በአገሪቱ በሚገኙ ሌሎች የኮቪድ-19 የሕክምና ማዕከሎች በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በጤና ሚኒስቴር በኩል ሲገለጽ ቆይቷል።
ጤና ሚኒስቴር እስካሁን በተደረጉ የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻዎች ክትባት የወሰዱት 24 ሚሊዮን 500 ሺህ ዜጎች ብቻ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ በትግራይ ክልል በአጋር ድርጅቶች አማካይነት የሚካሄደውን የክትባት ዘመቻ ጨምሮ 25 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ክትባት ለመስጠት መታቀዱን ገልጿል።
ወባ እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ
የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ከመግለጻቸው በተጨማሪ ስለ ወባ እና የዝንጀሮ ፈንጣጣም መረጃ ሰጥተዋል።
ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት እየተስፋፋ የመጣው የወባ በሽታ፣ ከ52 በመቶ በላይ በሚሆነው የኢትዮጵያ ክፍል እንዳለ በመግለጫው ተመልክቷል።
ለዚህም ምክንያቶቹ ለበሽታው መስፋፋት የሚሆን ምቹ የአየር ንብረት መኖሩ፣ በአገሪቷ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የመከላከል ሥራዎችን መሥራት ባለመቻሉ፣ የአጎበር አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ እጥረት ስላለ እንዲሁም ለተለያዩ የልማት ሥራዎች የተሠሩ የታቆሩ ውሃዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በሌላ በኩል፣ ከሰሞኑ ለዓለም አዲስ ስጋት በሆነው የዝንጀሮ ፈንጣጣ (መንኪፖክስ) የተያዘ ሰው እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ እንደሌለ ተገልጿል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር ባላት ግንኙነት ሳቢያ ከቫይረሱ ስጋት ነጻ እንዳልሆነችና ኅብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅም መግልጫው አያይዞ ጠቁሟል።












