ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በጥቃቷ በተገደሉት የረድዔት ሰራተኞች ላይ ሙሉ ሪፖርት ይፋ እንድታደርግ ተጠየቀች
እስራኤል በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በፈጸመችው ጥቃት ሰባት ሰራተኞቹ የተገደሉበት የረድዔት ድርጅት ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠየቀ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በተፈጸሙ “ከባድ ስህተቶች” የረድዔት ድርጅቱ ወርልድ ሴንትራል ኪችን ሰራተኞች ዒላማ ተደርገው ለሞት ተዳርገዋል ብሏል።
የእስራኤል ጦር ባደረገው ምርመራ ሁለት ከፍተኛ መኮንኖችን አባሯል።
የረድዔት ተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በበኩላቸው የእስራኤል ጦር “በጋዛ ውስጥ የራሱን ውድቀት በታማኝነት መመርመር አይችልም” ብለዋል።
ሥራ አስፈጻሚዋ ኤሪን ጎሬ “የእስራኤል መከላከያ ኃይል በባልደረቦቻችን ላይ በተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ይቅርታ መጠየቃቸው ደካማ ማጽናኛ ነው። ለተጎጂ ቤተሰቦችም ሆነ ለወርልድ ሴንትራል ኪችን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቂ አይደለም” ብለዋል።
የረድዔት ሰራተኞቹን ግድያ ተከትሎ በርካታ ተቋማት ሥራቸውን ያቆሙ ሲሆን እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ሰራተኞችን ደኅንነት ለማረጋገጥ “ተጨባጭ እርምጃዎችን” ልትወስድ ይገባል ሲሉ ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
እስራኤል አከናወንኩት ያለችውን እና ለሕዝብ ይፋ ያላደረገችውን የምርመራ ሙሉ ግኝትም እንድታትም ቁልፍ በሆኑ ምዕራባውያን አጋሮቿ ጫና እየተደረገባት ይገኛል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የእስራኤል ሪፖርት እንደደረሳቸው እና “በጥንቃቄ እየገመገሙት” እንደሆነ ገልጸዋል።
የባይደን አስተዳደር ለእስራኤል በሚሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ የተነሳ ከአንዳንድ ዲሞክራቶች ከፍተኛ ጫና እየገጠመው ይገኛል።
አርብ ዕለት የምክር ቤቱ የቀድሞ አፈ ጉባኤ የነበሩት ናንሲ ፔሎሲን ጨምሮ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ፕሬዚዳንት ባይደን እና ብሊንከን ለእስራኤል የሚደረገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ “እንዲያጤኑት” የሚጠይቅ ደብዳቤ ፈርመዋል።
ደብዳቤው የረድዔት ሰራተኞቹ የተገደሉበት የአየር ጥቃት ላይ ምርመራ እስኪደረግ ወይም እስራኤል በጋዛ ውስጥ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በበቂ ሁኔታ መቀነስ ካልቻለች አሜሪካ የጦር መሳሪያ መስጠቷን እንድታቆም ጠይቋል።
የእስራኤል ሚሳኤሎች ከቀናት በፊት ነበር በአራት ደቂቃ ውስጥ የእርዳታ ሰራተኞቹን የጫኑ መኪኖቹ ላይ አንድ በአንድ እየለዩ ጥቃት የፈጸሙት።
የበጎ እርዳታ ድርጅት ቡድኑ ከእስራኤል ዴይር አል ባላህ ከተሰኘው የእርዳታ ማከማቻ በባህር በኩል ለጋዛ የሚሆን ከ100 ቶን በላይ ምግብ ለማውረድ ፈቃድ አግኝቶ ነበር።
እርዳታውን አውርደው ሲወጡ ግን በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሲሆን የሐማስ ታጣቂዎች በሚልም መከላከያው አሳስቶ ዒላማ አድርጓቸዋል ተብሏል።