የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን መረጠ

የፎቶው ባለመብት, EOTC
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ አገረ ስብከቶች የሚመደቡ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን መምረጡን ይፋ አደረገ።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 28/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ክፍተት ባለባቸው፣ በተደራቢነት ተይዘው ለቆዩ እና ችግር አጋጥሟል ለተባሉ አገረ ስብከቶች ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጧል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ 18 ዕጩ ቆሞሳትን አቅርቦ በአብላጫ ድምጽ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጦ ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሠረት በቅርቡ ባረፉት በድሬዳዋው ጳጳስ አቡነ አረጋዊ ፈንታ፣ አባ ኃይለ ማርያም ጌታቸው ተመርጠዋል።
እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚገኙት ለምዕራብ አርሲ (አባ ሳህለማርያም ቶላ)፣ ለምሥራቅ ወለጋ (አባ ወልደ ገብርኤል አበበ)፣ ለምሥራቅ ሐረርጌ (አባ ጥላሁን ወርቁን) መርጧል።
በተጨማሪም ለሆሮ ጉድሩ ወለጋ (አባ አምደ ሚካኤል ኃይሌ)፣ ለምዕራብ ወለጋ (አባ ዘ ተክለኃይማኖት ገብሬ) ለቡኖ በደሌ (አባ እስጢፋኖስ ገብሬን) ኤጲስ ቆጶሳት ተደርገው ተመርጠዋል።
ከተሾሙት መካከል ከቤተ ክርስቲያኗ እውቅና ውጪ 26 ጳጳሳት ተሹመዋል ተብሎ ውዝግብ ካስከተሉት መካከልም የተወሰኑት እንደተካተቱበት ተገልጿል።
ባለፈው የካቲት ወር አቡነ ሳዊሮስን ጨምሮ ሦስት ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖና በጣሰ መልኩ 26 ጳጳሳትን በመሾማቸው ውዝግብ እና ከባድ ቀውስ ተከስቶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ይታወሳል።
ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪም በደቡብ ክልል አገረ ስብከት ለሚገኙት ለጌዶኦ፣ አማሮ እና ቡርጂ (አባ ክንፈ ገብርኤል ተክለማርያም) እንዲሁም ለዳውሮ ኮንታ (አባ ስብሐት ለአብ ኃይለማርያም) ኤጲስ ቆጶሳት ሆነው መመረጣቸው ተገልጿል።
የዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት በዓለ ሲመትም ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም. በቅዱስ ፓትርያርኩ ይፈጸማል ተብሏል።
የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ባለፈው ወር ግንቦት 14/ 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ውይይት ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት ለመምረጥ እና ለመሾም የስምምነት ውሳኔ ላይ መድረሱ ይታወሳል።
በዚህ ጉባዔ ላይ መወያያ የነበረው ዋነኛ ጉዳይ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሲሆን፣ ለኦሮሚያ ክልል 15 ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ቢቀርብ ስምምነት ላይ መደረስ አለመቻሉ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
በመጨረሻም ለድሬዳዋ፣ ለኦሮሚያ ክልል እና ለደቡብ ክልል አገረ ስብከቶች ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ስምምነት ላይ ተደርሶ ኮሚቴ በመሰየም ተጠናቋል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ከሳምንት በላይ በፈጀው በዚህ ጉባኤው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት አስመራጭ ኮሚቴ የሰየመ ሲሆን፣ እነሱም ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ (ከሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ)፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ (ከሐዲያ ከምባታ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) እና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ (ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ይገኙበታል።
ከቅርብ ወራት በፊት ከፓርትርያርኩም ሆነ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጭ 26 ጳጳሳት መሾማቸውን ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት እና ቀኖና የሚጥስ ነው በማለት የጵጵስና ማዕረጉን የሰጡትን እንዲሁም የተሾሙትን የማውገዝና ሹመታቸውም ተሽሮ እንዲለዩ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።
የቤተ ክርስቲያኗ አካሄድ አካታች እንዳልነበረ እና ምዕመናን በቋንቋቸው መገልገል እንዳልቻሉ በመግለጽ አዲስ ሲኖዶስ መቋቋሙን የገለጹት ጳጳሳት፣ ውሳኔውን በማውገዝ በእርምጃቸው እንደሚቀጥሉም በወቅቱ አስታውቀው ነበር።
ለእምነቱ መስፋፋት እንቅፋት የሆኑ ናቸው የተባሉ የቋንቋ እና የአሳታፊነት ጉዳይን ባነሱ አባቶች አማካይነት በቤተከርስቲያኗ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ተፈጥሮ፣ ከሳምንታት ውዝግብ እና ፍጥጫ እንዲሁም የሰው ሕይወት አስከጠፋባቸው፣ እስራትን ካስከተሉ ክስተቶች በኋላ በስምምነት እልባት ማግኘቱ ይታወሳል።












