ሱቶን ሊቨርፑል በኒውካስል ይሸነፋል፤ ቼልሲ የመጀመሪያውን 3 ነጥብ ያገኛል ሲል ገመተ

ታትሟል

3ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ።

ስድስት ጨዋታዎች ቅዳሜ ሲከናወኑ ቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች እሑድ እንዲከናወኑ መርሃ ግብር ወጥቶላቸዋል።

ኒውካስል በሜዳው ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት የእሑድ ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን ይህንን ጨዋታ ጨምሮ ሁሉንም ጨዋታዎችም እንደሚከተለው ገምቷል።

አርብ

ቸልሲ ከ ሉቶን

ቼልሲ ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ነው ያሳካው።

ካለፈው ዓመት ቡድን አንጻር ቼልሲ የተሻለ ፍሰት ያለው ሲሆን ራሂም ስተርሊንግም የተሻሻለ ተጫዋች ሆኖ ቀርቧል።

ከሉቶን ደካማ አጀማመር አንጻር የውድድር ዓመቱ ረዥም የሚሆንበት ይመስላል።

ቼልሲ ላይም ጎል ያስቆጥራሉ ብዬ አላስብም።

ግምት፡ 3 – 0

ቅዳሜ

ቦርንመዝ ከ ቶተንሃም

አንጅ ፖስተኮግሉ ከወዲሁ ቶተንሃምን እንዲሻሻል አድርገዋል። የቡድኑ መሻሻል የሚወሰነው ግን በጀምስ ማዲስን ከጉዳት ነጻ መሆን ነው።

ቦርንመዝ ከሊቨርፑል ጋር ጥሩ አጀማምር ቢያደርግም አልተሳካለተም።

በዚህ ጨዋታ ቶተንሃም ሦስት ነጥቡን ያሳካል።

ግምት፡ 1 – 2

አርሰናል ከ ፉልሃም

አርሰናል ሰኞ ዕለት ከክሪስታል ፓላስ ድንቅ ሦስት ነጥብ አሳክቷል። ዘንድሮ ድንቅ ብቃታቸውን ባያሳዩም ጥሩ አጀማመር አድርገዋል።

ፉልሃም በመጀመሪያው ሳምንት ኤቨርተንን ቢያሸንፍም በብሬንትፎርድ ደግሞ ተሸንፏል።

ይህንን ጨዋታ በቀላሉ ባለሜዳዎቹ መድፈኞቹ ያሸንፋሉ።

ግምት፡ 3 – 0

ብሬንትፎርድ ከ ክሪስታል ፓላስ

ብሬንትፎርድ ባለፈው ዓመት በሜዳው ጥሩ ነበር።

ቡድኑ አይቫን ቶኒን በቅጣት ቢያጣም ዮአን ዊሳ እና ብሪያን ምቡሞ ቦታውን እየሸፈኑ ነው።

ብሬንትፎርድ የተቀናጀ ቡድን ቢሆንም ፐላሰም በሮይ ሆድሰን ስር ተሻሽሎ ቀርቧል።

ይህንን ጨዋታ ብሬንትፎርድ ያሸንፋል።

ግምት፡ 1 – 0

ኤቨርተን ከ ዎልቨስ

ኤቨርትን ከፉልሃም ጋር ጥሩ ቢጫወትም ተሸንፏል። ከአስቶን ቪላ ጋር ደግሞ ጥሩ አልነበረም።

ዎልቭስ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ጥሩ የነበረ ቢሆንም በብራይተን ደግሞ ተበልጧል።

ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች አስፈላጊ ነው።

ሁለቱም ቡድኖች ጎል እንደሚያስቆጥሩ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 – 1

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ማንቸስተር ዩናይትድ ያልተቀናጀ ቡድን ከመሆኑም በላይ በፈጠራ በኩልም ደካማ ነው።

ኖቲንግሃም ፎረስት ባለፈው ዓመት ከሜዳው ውጭ ደካማ ከመሆኑም በላይ የበርናን ጆንስ ስም ከስፐርስ ጋር ተያይዟል።

ይህ ጨዋታ ለማንቸስተር ነገሮችን የሚቀይሩበት ነው።

ጨዋታውንም እንደሚያሸንፉ አስባለሁ።

ግምት፡ 3 – 1

ብራይትን ከ ዌስት ሃም

ይህ ጨዋታ ምን እንደሚመስል የምናውቅ ይመስለኛል።

ብራይተን በማጥቃት፤ የዴቪድ ሞዬስ ቡድን ደግሞ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ይመርጣል።

ብራይተን ድንቅ አጀማምር አድርጓል። በዚህ ጨዋታም ዕድሎችን ፈጥሮ ጎሎችን ያስቆጥራል።

ግምት፡ 2 – 0

እሑድ

በርንሌይ ከ አስቶን ቪላ

በርንሌይ ባለፈው ሳምንት ጨዋታውን አላከናወነም።

ከማንቸስተር ሲቲ ሽንፈት በኋላ ይኼኛውም ጠንካራ ጨዋታ ይሆንባቸዋል።

ካሳዩት አጨዋወት አንጻር ውጤታማ አይሆኑም ባይባልም አስቶን ቪላ የተሻለ በመሆን ሦስት ነጥቡን ያሳካል።

ግምት፡ 1 – 2

ሼፊልድ ዩናይትድ ከ ማንቸስተር ሲቲ

ሼፊልድ ዩናይትድ ትልቅ አደጋ ውስጥ ነው። ከኖቲንግ ሃም ጋር ጥሩ ቢፎካከሩም ተሸንፈዋል።

በክሪስታል ፓላስም በተመሳሳይ ሽንፈትን አስተናግደዋል። ሦስተኛው ተጋጣሚያቸው ደግሞ ኃያሉ ሲቲ ነው።

ጨዋታውን ማንቸስትር ሲቲ ያሸንፋል።

ግምት፡ 0 – 4

ኒውካስል ከ ሊቨርፑል

ኒውካስል በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ አስቶን ቪላን ማሸነፍ ችሏል።

ከማንቸስተር ሲቲ ጋርም ጥሩ ፉክክር አድርገዋል። የሊቨርፑል የአጥቂ መስመር በድንቅ ተጫዋቾች የተሞላ ነው።

ለመሆኑ ቡድኑ ይህንን የአጥቂ መስመር የሚያግዝ አማካይ አለውን?

ግምት፡ 3 – 1