ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለከንቲባነት ተመረጡ
የቀድሞው የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ሮድሪጌ ዱቴርቴ ኔዘርላንድ ዘ ሄግ ውስጥ በእስር ላይ እያሉ በተደረገ ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት የአገሪቱ አንድ ከተማ ከንቲባ ለመሆን ተመረጡ።
የድሞው ፕሬዝድንት ፊሊፒንስን እየመሩ በነበረበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተገደሉባቸው ፀረ አደንዛዥ ዕጽ ዘመቻዎች ወቅት በሰብአዊነት ላይ ተፈጽመዋል በተባሉ ወንጀሎች ተከሰው ከአገራቸው ተይዘው በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
ባለፈው መጋቢት ወር ከአገራቸው ዋና ከተማ ማኒላ ተይዘው ወደ ኔዘርላንድስ የተወሰዱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትናንት ሰኞ በተካሄደው ምርጫ ከተቆጠሩት 80 በመቶ ድምጾች አብዛኛውን ለማግኘት ችለዋል።
ዱቴርቴ እና ቤተሰባቸው በደቡባዊ ፊሊፒንስ የምትገኘው ደሴት ከተማ የሆነችው የዳቫዎ ከንቲባነትን ቦታ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚነት ሲያሸነፉ ቆይተዋል።በአሁኑ ምርጫ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከተፎካካሪያቸው ስምንት እጥፍ የሚልቅ ድምጽ አግኝተው ማሸነፋቸው እየተዘገበ ነው።
የ80 ዓመቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሁን እየተካሄደ ባለው የምርጫ ዘመን አጋማሽ ላይ በተካሄደው ምርጫ ማሸነፋቸው በከተማዋ ውስጥ ያላቸውን ተጽእኖ ያመለክታል ተብሏል።
ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2022 ለስድስት ዓመታት የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ሆነው በሠሩበት ጊዜ በወንጀል እና በዕጽ ዝውውር ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድ የሚታወቁት ዱቴርቴ ባሸነፉባት ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ዝናን አትርፈዋል።
በወንጀል እጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች ላይ እንዲወሰድ ባደረጉት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ የሙገሳ ቅጽል ስሞትች ያገኙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከሕግ ውጪ የሚወሰዱ ናቸው ባሏቸው እርምጃዎች ሲከሰሱ ቆይተዋል።
በፊሊፒንስ ፖለቲካ ውስጥ ተጽእኖ ያላቸው ሮድሪጌ ዱቴርቴ ብቻ ሳይሆኑ ልጆቻቸውም ጭምር በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና አላቸው።
ሴት ልጃቸው ሳራ ዱቴርቴ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆኑ በቀጣይ ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር እየተዘጋጁ እንደሆነ ይነገራል።
ወንድ ልጃቸው ሴባስቲያን ዴቴርቴ ደግሞ አባታቸው ያሸነፉበት ከተማ ከንቲባ የነበሩ ሲሆን አሁን ለምክትል ከንቲባነት ተመርጠዋል።
እየተካሄደ ባለው የምርጫ ዘመን አጋማሽ ምርጫ ላይ የተለያዩ ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ውድድር እየተደረገባቸው ሲሆን የቀድሞው ፕሬዝዳንት አጋሮች ተጨማሪ ቦታ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ ያላቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮድሪጌ ዱቴርቴ ከአገራቸው ተይዘው ወደ ኔዘርላንድስ ከተወሰዱ ከሁለት ወራት በኋላ በተካሄደው ምርጫ እስካሁን በተቆጠረው ድምጽ የእሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው ጠንካራ ይዞታቸው በሆነው በደቡባዊ የፊሊፒንስ ክፍል የበላይነታቸውን አጠናክረዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከዋና ከተማዋ ማኒላ ተይዘው ወደ አውሮፓ ፍርድ ቤት የተወሰዱት ሴት ልጃቸው ምክትላቸው የሆኑት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ማርኮስ ጁኒየር ፈቃድ ሰጥተው በመሆኑ በምክትላቸው እና በፕሬዝዳንቱ መካከል ቅራኔን አባብሶታል።
በዚህም የተነሳ የዱቴርቴ ሴት ልጅ እንዲከሰሱ የፕሬዝዳንቱ አጋሮች በአገሪቱ ምክር ቤት ውስጥ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበው አጸድቀዋል። የዱቴርቴ ሴት ልጅ እና የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳራ ዱቴርቴ የቀረበባቸው ክስን "ፖለቲካዊ ነው" ሲሉ ተቃውመውታል።
ታዋቂዋ ምክትል ፕሬዝዳንት በ2028 በሚካሄደው ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት ይወዳደራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ነገር ግን የቀረቡባቸው ክሶች ተቀባይነት ካገኙ ግን ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሊታገዱ ይችላሉ።
አሁን ለከንቲባነት የተመረጡት አዛውንቱ ዱቴርቴ በአውሮፓውያኑ የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት ዳቫዎ ከተማን ለ20 ዓመታት በከንቲባነት መርተዋል። በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው የካሄዱት የፀረ አደንዛዥ እጽ ጦርነት ስኬታማ እንደነበር ይነገርለታል።
ከአገራቸው ውጪ በእስር ላይ ሳሉ ለከንቲባነት የተመረጡት የዱቴርቴ ልጅ ሴባስቲያን በምክትል ከንቲባነት ስለተመረጡ የአባታቸውን ኃላፊነት ተረክበው ሊሠሩ ይችላሉ።
ሴት ልጃቸው የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ከአጋሮቻቸው ጋር የምክር ቤት መቀመጫዎችን ለመቆጣጠር እየተፎካከሩ ሲሆን፣ ሌላኛው ወንድ ልጃቸው ፓውሎ ደግሞ ለምክር ቤት አባልነት በድጋሚ ተመርጠዋል።
ሌሎች የልጅ ልጆቻቸውም በአካባቢያዊ ምርጫዎች ለማሸነፍ መቻላቸው ተነግሯል።