የደቡብ አፍሪካው ቱጃር ቤተሰብ አባላት ኤምሬትስ ውስጥ ታሠሩ

ዙማና አቱል ጉፕታ

የፎቶው ባለመብት, SOUTH AFRICAN GOVERNMENT

ታትሟል

የደቡብ አፍሪካው ቱጃር ቤተሰብ ሁለት ወንድማማቾች ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ (ዩኤኢ) ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

አቱል እና ራጄሽ ጉፕታ ከቀድሞው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ ጋር ተመሳጥረው ሃብታቸውን አበልፅገዋል ተብለው ይፈለጋሉ።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት ደቡብ አፍሪካ ወንድማማቾቹን ለማምጣት ከዩኤኢ ጋር መምከር ጀምራለች።

አቱልና ራጄሽና ከደቡብ አፍሪካ ሹልክ ብለው የወጡት በፈረንጆቹ 2018 የሙስና መዝገብ ተከፍቶ ምርመራ በተጀመረ ወቅት ነው።

የጉፕታ ወንድማማቾች የሚፈልጓቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሾሙ ገንዘብ ሰጥተዋል፤ ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ አባብለው የራሳቸው አድርገዋል ተብለው ይከሰሳሉ።

የጉፕታ ቤተሰብ ከሕንድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናው በፈረንጆቹ 1993 ነው።

ይህ ቤተሰብ የሕንዷ ዋና ከተማ ኒው ደልሂን ጨምሮ በሌሎች የሕንድ ከተሞች በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ በማዘዋወር ይፈለጋል።

ሕንድ በተወለዱት ሁለቱ ወንድማማቾች ላይ የሚቀርበው ጠንከር ያለው ክስ በጃኮብ ዙማ የሥልጣን ዘመን ሠርተዋል በሚባለው ነው።

የጉፕታ ቤተሰብ ከዙማ ጋር ያላቸውን የቅርብ ግንኙነት ተጠቅመው የፖለቲካ ምሕዳሩን ዘውረዋል፤ ከበድ ያሉ የቢዝነስ ስምምነቶችን ተቆጣጥረዋል፤ በመንግሥት ሥራ ጣልቃ ገብተዋል ይባላሉ።

ፕሬዝደንት ዙማም ሆኑ የጉፕታ ቤተሰብ ክሱን ያጣጥላሉ።

ደቡብ አፍሪካ ወንድማማቾቹን ከዩኤኢ ለማምጣት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ድርድር ስታደርግ ቆይታለች።

የወቅቱ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ወንድማማቾቹ ችሎት ፊት ይቀርባሉ ይላሉ።

ነገር ግን የጉፕታ ወንድማማቾች ወደ ደቡብ አፍሪካ ይመለሱ አይመለሱ ግልፅ አይደለም።

የጉፕታ ቤተሰብና ዙማ በጣም ከመቀራረባቸው የተነሳ "ዙፕታ" የተሰኘ ቅጥል ስም ተበጅቶላቸው ነበር።

ከዙማ ሚስቶች መካከል አንዷ እንዲሁም ወንድና ሴት ልጆቻቸው በጉፕታ ቤተሰብ ኩባንያዎች ውስጥ ትላልቅ ቦታ ይዘው ይሠሩ ነበር።

ባለሥልጣናት ከጉፕታ ቤተሰብ ቀጥታ ትዕዛዝ መጥቶ ውሳኔ እንድንሰጥ ተገደን እናውቃለን ሲሉ በይፋ ተናግረው ያውቃሉ።

የገንዘብ ሚኒስቴርና የደቡብ አፍሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤስኤቢሲን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ ኤርዌይስ እንዲሁም የባቡር ትራንስፖርት ከጉፕታ ቤተሰብ ጋር ተያይዞ ስማቸው ከሚነሳ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

የደቡብ አፍሪካው ጉምቱ ዳኛ አራት ዓመት የፈጀውን ምርመራ ውጤት ይፋ ሲያደርጉ የጉፕታ ቤተሰብ ገዥው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲን ሲዘውሩ ነበር ብለዋል።

ዙማ ባለፈው ዓመት የጉፕታ ቤተሰብ ላይ አልመሰክርም ብለው በ15 ወራት እሥራት ተቀጥተው ነበር።

አጃይ፣ አቱልና ራጄሽ ጉፕታ ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡት ከአፓርታይድ መውደቅ በኋላ በፈረንጆቹ 1993 ነበር።

በኮምፒውተር ንግድ የጀመረው ሥራቸው ተጧጡፎ በደቡብ አፍሪካ የሚጠቀሱ ባለሀብት ቤተሰብ እስከመሆን ደርሰዋል።