ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቬንዝዌላ ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር 235 ደረሰ
በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ አቅራቢያ በደረሱ ሁለት ተከታታይ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጦች ቢያንስ የ235 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 4,300 የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው።
የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ከፍርስራሾች ውስጥ ሰዎችን ለማውጣት ጥረት እያደረጉ ነው።
በካራከስ እና በአቅራቢያው በሚገኛው የባሕር ዳርቻ ከተማ ላ ጉኣራ በሕንፃዎች ፍርስራሽ የተቀበሩ ሰዎች ለእርዳታ ሲጣሩ ይሰማሉ።
የመጀመሪያው እና በርዕደ መሬት መለኪያ 7.2 የተለካ አደጋ ከበድ ያለ 7.5 የመሬት መንቀጥቀጥ የተከተለው ሲሆን፤ እንደ አሜሪካ ጅኦሎጂካል ሰርቬይ ከሆነ የመሬት መንቀጥቀጦቹ ከመሬት ቀረብ ብለው የተከሰቱ በመሆናቸው ውድመቱን ከባድ አድርጎታል።
በአደጋው በርካታ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ ሲገመት፤ ሌሎች ደግሞ ቤት አልባ ወይንም በተጎዱ እና ለአደጋ በተጋለጡ ሕንፃዎች ውስጥ ከመቆየት ይልቅ መንገድ ላይ መሆንን መርጠዋል።
አደጋው የደረሰው ዕረቡ ዕለት ቬንዙዌላ ብሔራዊ በዓል እያከበረች በነበረችበት ጊዜ ነው። ይህም ማለት አደጋው የደረሰው ከወትሮ በተለየ በርካታ ሰዎች ቤት ውስጥ እያሉ ነበር።
የቬንዙዌላ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆርሄ ሮድሪጉዝ የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ አስቸኳይ ጊዜ ካወጁ በኋላ የሟቾች ቁጥር መጨመሩን አስታውቀዋል።
የነፍስ አድን ሥራውን ለማገዝ በርካታ አገራት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡ ሲሆን፤ አሜሪካ 150 ሚሊዮን ዶላር ለእርዳ እንደምትሰጥ አስታውቃለች። የአሜሪካ ጦር የነፍስ አድን ሠራተኞችን ለማገዝ እና "ፈጣን የእርዳታ" ለማድረግ የመጓጓዣ መርከቦችን እና አውሮፕላኖችን መላኩን አስታውቋል።
ሆርሄ ሮድሪጌዝ 250 ሕንፃዎች እንደተጎዱ አሊያም እንደወደሙ ተናግረዋል። በተለይም በላ ጉኣራ ቢቢሲ ባረጋገጣቸው ምሥሎች ባለ 10 ወለል ሆቴል ፈርሷል። ሐሙስ ዕለት ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ሲፈልጉ ነበር።
ኋን ኦርቴዝ የተባለው ግለሰብ የቅርብ ጓደኛው መሞቱ እንደተረጋገጠ፤ ሌላኛው ጓደኛው ደግሞ በፍርስራሹ ውስጥ እንደተቀበረ እንደሚታመን ለቢቢሲ ተናግሯል። በባሕር ዳርቻ አካባቢዎች የሚኖሩ 20 የሚሆኑ የሚያውቃቸው ሰዎች ደግሞ እንደጠፉ ገልጿል።
"በድንጋጤ እና ግርታ ውስጥ ነኝ፤ መርዳት ባለመቻሌ ተበሳጭቻለሁ" ብሏል በካራከስ የሕክምና ተማሪ የሆነው ኋን።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኣሶዳዶ ካቤሎ በዋና ከተማዋ ካራከስ ሕንፃዎች መውደቃቸውን እና አንዳንድ አካባቢዎችም እንደተጎዱ ተናግረዋል።
ከካራከስ ወጣ ብሎ የሚገኘው የቬንዙዌላ ዋና ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ምክንያት መዘጋቱን የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አስታውቀዋል። ከመንገደኞች ማስተናገጃ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ከጣራው ፍርስራሾች እና አቧራ ሲረግፍ አሳይተዋል።
ከካራከስ ሰሜን ምዕራብ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው እና ቱካካስ ሆቴል ነው የተባለ በርካታ ወለሎች ያሉት ሕንፃ መውደሙን የሚያሳይ የተረጋገጠ ተንቀሳቃሽ ምሥል አሳይቷል።
ከርዕደ መሬቱ በኋላ በአካባቢዎቹ ድኅረ መንቀጥቀጥ የቀጠለ ሲሆን፤ ቢያንስ 30 ንዝረቶች መሰማታቸውን ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ለአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።
ከ10 ሺ በላይ ሰዎች ሊሞቱ የሚችሉበት ዕድል 42 በመቶ ላይ የተገመጠ ሲሆን፤ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች የመሞት ዕድላቸው ደግሞ 33 በመቶ መሆኑ ተገምቷል።
ካቤሎ አታሚራ እና ሎስ ፓሎስ ግራንዴስ የተባሉ የካራከስ ሰፈሮች ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው ብለዋል።
እነዚህ አካባቢዎች 200 ሰዎች በሞቱበት የአውሮፓውያኑ 1967 የመሬት መንቀጥቀጥ ከሌሎች አካባቢዎች በበለጠ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።
ከቀናት በፊት ቬንዙዌላን የመታት ሁለተኛው ርዕደ መሬት ከ1900 ወዲህ ከባዱ እንደሆነ የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ ያሳያል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኒኮላስ ማድሮን ባለፈው ጥር በቁጥጥር ስር ካዋሉ ወዲህ አደጋው ለቬንዙዌላ አዲስ መሪዎች የመጀመሪያ ፈተና እንደሚሆን ይታመናል።